በቴል አቪቭ የነበረ አመጽ

6 መስከረም 2023, 12:44 EAT

ተሻሽሏል 6 መስከረም 2023, 12:45 EAT

የኤርትራ መንግሥት በእስራኤል በባሕል ፌስቲቫል ላይ በተከሰተው ሁከት የተሳተፉት እንደ ሞሳድ ባሉ የደኅንነት ተቋማት የተደገፉ ናቸው አለ።

የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርወቂ መንግሥት ይህን ያለው በቅርቡ በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ በኤርትራ መንግሥት እና ተቃዋሚዎች መካከል ከፍተኛ ግጭት ተከስቶ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው።

ከሁከቱ በኋላ የእስራኤል መንግሥት በተለይ የኤርትራ መንግሥትን ደግፈው በአደባባይ ሁከት የተሳተፉትን ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገራቸው አባርራለሁ ሲል ዝቷል።

ቅዳሜ ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. በቴል አቪቭ በነበረው ሁከት ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በሁለት ጎራ ተከፍለው ሁከት ፈጥረው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አፍሪካውያን ስደተኞች በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር እቅድ እንዲወጣ አዘው ነበር።

የእስራኤል ፖሊስ ሁከቱን ለመቆጣጠር ጥይት፣ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ኤርትራውያን ላይ ለመተኮስ ተገዷል።

የባሕል ፌስቲቫሉን የሚቃወሙት ሥነ-ስርዓቱ ለአምባገነኑ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ነው ይላሉ።

የኤርትራ መንግሥት ግን በኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በኩል ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የኤርትራውያንን ብሔራዊ ማንነት የሚያስቀጥሉ ፌስቲቫሎች እንደ ሞሳድ ባሉ የእስራኤል ደኅንነት መሥሪያ ቤት የሚደገፉ ሁከት ፈጣሪዎች እንዲጨናገፍ እየተደረገ ነው” ብሏል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአውሮፓ ከተሞች አና በሌሎች ስፍራዎች “በኤርትራውያን ማኅብረሰብ አባላት የተዘጋጁ ፌስቲቫሎች በተደራጁ ቡድኖች ሲታወኩ እና ንብረት ሲወድም ተመልክተናል” ብሏል የኢንፎርሜሽን ሚንሰቴሩ።

የኤርትራ መንግሥት “የእነዚህ ድርጊቶች ዋነኛ ዓላማ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ማንነታቸው እና አገራዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት ማደናቀፍ ነው” ብሏል።

ሚኒስቴሩ የኤርትራ መንግሥት በመቃወም ከመንግሥት ደጋፊዎች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች የእስራኤል የደኅንነት ተቋም የሆነው ሞሳድን ጨምሮ በሌሎች የደኅንነት ኤጀንሲ ይደገፋሉ ይበል እንጂ ለዚህ ማስረጃ አላቀረበም።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠር መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

በዚህ ዓመት ብቻ በእስራኤል ጨምሮ በጀርመን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና በካናዳ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል ይላሉ።

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካቶች ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።