
13 መስከረም 2023
ከአሜሪካ ፔንስልቪንያ እስር ቤት አምልጦ ሲታደን የነበረው ታራሚ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የ34 ዓመቱ ዳኔሎ ካቫልካንቴ በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊሶች ክትትል ሲያደርጉበት በነበረ ጫካ ውስጥ እንደሆነም የህግ አስከባሪ ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የብራዚል ዜግነት ያለው ታራሚ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከእስር ቤት ያመለጠ ሲሆን እሱንም አድኖ ለመያዝ ከ500 በላይ የፖሊስ መኮንንኖች ተሰማርተው ነበር።
ግለሰቡ ከሁለት ዓመታት በፊት የቀድሞ ፍቅረኛውን በሁለት ህጻናት ልጆቿ ፊት በመግደል ወንጀል እስር የተበየነበት ባለፈው ወር ነበር።
ፖሊስ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ላይ ግለሰቡ የተያዘበትን ዝርዝር ሁኔታም ያካፍላል ተብሎ ይጠበቃል።
ታራሚው በፖሊስ መኪና ውስጥ ሲጫን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች አጋርተዋል።
ዳኔሎ ከዚህ ግድያ በተጨማሪም በትውልድ አገሩ በተፈጸመም ግድያ ጋርም በተያያዘ እንደሚፈለግም ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ፖሊስ ከቦት ከነበረው ስፍራም ማምለጡም ተዘግቧል።
የቼስተር ካውንቲ ነዋሪዎችም ግለሰቡ በተደጋጋሚ በአካባቢው ታይቷል መባሉ ጋር ተያይዞ ስጋት ገብቷቸው እንደነበርም ተገልጿል።
- ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን ሳተላይት በጦር መሳሪያ ሊቀያየሩ ነው ተባለ13 መስከረም 2023
- ሪፓብሊካኖች ጆ ባይደንን ከስልጣን ለማውረድ ምርመራ እንደሚከፍቱባቸው አስታወቁ13 መስከረም 2023
- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግብጽን እና ሱዳንን ለምን ያሰጋቸዋል?12 መስከረም 2023
ፖሊስ ከማረሚያ ቤት ያመለጠው ነፍሰ ገዳይ 22 ካሊበር ጠመንጃ ከአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሰርቋል ሲልም በዚህ ሳምንት ማክሰኞ አስጠንቅቆ ነበር።
ነገር ግን የፔንስልቬንያ አስተዳዳሪ ቆይተውም ተልዕኮው እንደተጠናቀቀ እና ታራሚውም እጅ እንዲሰጥም አሳስበው ነበር።
የሟቿ ዲቦራ ብራንዶ ቤተሰቦች ግለሰቡ ሊያጠቃቸው ይችላል በሚል ስጋትም ፖሊስ የ24 ሰዓት ክትትል ሲያደርግላቸው ቆይቷል።
የታራሚው እናት ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ያልተለመደ ቃለ ምልልስ ልጃቸው በህይወት ለመቆየት እየታገለ እንደሆነ እና “ለማንም ስጋት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ልጄ ያደረገው ስህተት እንደሆነ አውቃለሁ። ልጄ ለጥፋቱ መክፈል እንዳለበት አውቃለሁ” በማለት እናቱ ኢራሴማ ካቫልካንቴ ተናግረዋል።
“ሆኖም ልጄ ለስህተቱ በክብር እንዲከፍል እፈልጋለሁ። በህይወቱ መክፈል የለበትም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ታራሚው የቀድሞ ፍቅረኛውን ዲቦራን ከመግደል በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2017 በብራዚል ባልተከፈለ ዕዳ ምክንያት አንድ ጓደኛውንም በመግደል ክስ ቀርቦበታል።
