
ከ 4 ሰአት በፊት
በደቡብ አፍሪካዋ መዲና ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በትግራይ የጠመንጃ አፈሙዞች ጸጥ እንዲሰኙ አድርጓል።
ስምምነቱ ለመቶ ሺዎች ሞት ምክንያት የሆነው ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ቋጭቷል። ፈርሶ የነበረውን የትግራይ አስተዳደር እንዲመለስ አድርጓል።
በሁለቱ አካላት ስምምነትም መሰረት ከዚህ ቀደም ትግራይ በተናጠል ያደረገችው ምርጫ ተሰርዞ በክልሉ ምርጫ እስኪደረግ፣ የጊዜያዊ መንግሥትም እንዲመሰረት ተወሰነ።
የፕሪቶሪያው ስምምነት መመስረት ሁለቱ ተፈራራሚ ወገኖች ጊዜያዊ መንግሥት እንደሚያቋቁሙ ይጠቅሳል።።
ሆኖም ጊዜያዊ መንግሥት ምስረታውን ከሚያቋቁመው ኮሚቴ እንዲሁም ከሰነድ ዝግጅቱ ጀምሮ የገለልተኝነት እና የአሳታፊነት ጥያቄ በማንሳት ከትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።
የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጊዜያዊ መንግሥት የሚመሰርተውን አስተባባሪ ኮሚቴን ህወሓት ብቻውን ያቋቋመው በሚል እንደማይቀበሉት እንዲሁም በህዝባዊ ውይይቶችም ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው ይታወሳል።
በክልሉ ሁሉን አካታች መንግሥት ለመመስረት ወራት የፈጀ ሲሆን ሂደቱን የተቃወሙ እንደ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት)፣ የትግራይ ነጻነት ድርጅት (ውናት) እንዲሁም የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲዎች ራሳቸውን አግልለዋል።
ህወሓት የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑትን ዶ/ር ደብረጽዮን ጊዜያዊ መንግሥቱን እንዲያስተዳድሩ ፕሬዚዳንት አድርጎ ቢመርጣቸውም በፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት እንዳልተገኘ በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተንታኞች ገልጸው ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ “አዲስ አመራር አምጡ” በማለቱ በድርጅቱ ውስጥ ፓለቲካዊ ሽኩቻ እንዳጋጠመ እና ለመዘግየቱ ምክንያት እንደሆነም እነኚሁ ተንታኞች ተናግረዋል።
ፓርቲው ዳግመኛ ባካሄደው ምርጫ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ተፎካካሪያቸውን በአንድ ድምጽ በመብለጥ በማሸነፋቸው መጋቢት 14/ 2015 ዓ.ም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው በጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ተሾሙ።
አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳዳሪነቱን ስፍራም ከተቆናጠጡ በኋላ “የትግራይ ግዛቶች እንደሚመለሱ እንዲሁም ተፈናቃዮች በአጭር ጊዜ ወደቦታቸው” ለመመለስ እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
ሆኖም የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት መዘግየቱን ባለፈው ሳምንት ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ጌታቸው “መንግሥታቸው በክልሉ ውስጥም ተቀባይነት አለማግኘቱን” ተናግረዋል።
እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አፈጻጸም ጉልህ ክፍተቶች እንዳሉበት ‘አፍሪካንስ ፎር ዘ ሆርን’ የተሰኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረት ከሁለት ወራት በፊት ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል።
በትግራይ ውጊያው ቢቆምም “በውጭ ኃይሎች” በተያዙ አካባቢዎች አሁንም የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል ብሏል።
እነዚህም በኤርትራ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች እና የአማራ ኃይሎች በሚቆጣጠሩት የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች መሆኑም ተጠቅሷል።
የኤርትራ ኃይሎች የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላ ግድያዎችና ወሲባዊ ባርነቶችን ጨምሮ የጦር ወንጀሎችን መፈጸማቸውን አምነስቲ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።
በምዕራብ ትግራይም እንዲሁ ከስምምነቱ በኋላ የአማራ ኃይሎች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመተባበር የዘር ማጽዳት ወንጀል መፈጸማቸውን ሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት አውጥቷል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው አለመመለስ እንዲሁም ስምምነቱን የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ የባለሙያዎች ቡድን እየተፈጸሙ ያሉ ጥሰቶችን በይፋ ሪፖርት የሚያደርግበት ስልጣን አለመኖርም ክፍተቶች አሉበት ብሏል።
- ባይደን የሰሜን ኢትዮጵያው ሁኔታ ባለመሻሻሉ ያስተላለፍኩት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ እንዲራዘም ወስኛለሁ አሉ8 መስከረም 2023
- ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ወሲባዊ ባርነት እና ግድያዎችን ፈጽመዋል-አምነስቲ5 መስከረም 2023
- በግጭቶች እየተፈተነ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት እያመራ ነው?29 ነሐሴ 2023
ለመሆኑ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስካሁን ምን ሰራ? ምንስ ተግዳሮቶች እየገጠሙት ነው?
በክልሉ ጊዜያዊ መንግሥት ምስረታ ወቅት ፍትሃዊ ውክልና አልተደረገም በማለት የተሰጠውን ኮታ ያልተቀበለው የሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ከበደ ጊዜ አስተዳደሩ እስካሁን “ምንም አልሰራም” ይላሉ።
“የመንግሥት፣ የሽግግርም ይሁን ቋሚ የመጀመርያው ኃላፊነቱ የሕዝብን ደህንነት እና ጸጥታ መጠበቅ ወይ በሕግ የተሰጠው ስልጣን መፈጸም ነው። የመጀመርያው ስራ የክልሉን ሉዓላዊነት መመለስ እንዲሁም የክልሉን ደህንነት እና ጸጥታ መጠበቅ ነው“ ይላሉ።
ይህ ግን በትግራይ ተፈጻሚ እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ኃይሉ
“የጫካ ሽፍቶች የሕዝብን ከብት እየሰረቁ እያረዱ ነው። የከተማ ሽፍቶችም ታርጋ የሌላቸው መኪኖች እያሽከረከሩ ሕዝቡን በመግደል እና በመዝረፍ ላይ ናቸው። “ በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።
በኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ግጭት ጥናት ፕሮፌሰር እና የቀጠናው ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሸቲል ትሮንቮል በበኩላቸው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነቱ እንዳይጣስ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል ይላሉ።
“ ያስገኘው ትልቅ ነገር፣ ግጭት የማቆም ስምምነት ትግበራ እንዲቀጥል ማድረጉ ነው። በፌደራል መንግሥቱ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ በመሆኑ ወደ ግጭት አልተመሰሱም። ፈጣን ባይሆንም በግጭት የማስቆም ስምምነቱ ላይ የተቀመጡት መርሆች ትግበራ እየቀጠለ ነው” ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት መሰረታዊው ነገር በፌደራል እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያለው ንግግር አለመቋረጡ እና በአዲስ አበባ እና መቀለ መካከል ያለው ሰላማዊ ግንኙነት መቀጠሉ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ጦርነቱን ተከትሎ የአማራ ኃይሎች የተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ አስዳደሩ እስካሁን ማስመለስ አለመቻሉን የሚገልጹት ፕሮፌሰር ትሮንቮል ይህም ቢሆን ከአስተዳደሩ ስልጣን በላይ መሆኑ ያስረዳሉ።
“እንዲፈጸሙ የሚጠበቁ ብዙ ነገሮች አሉ። ከነዚህ ዋነኛው የትግራይ ግዛታዊ አንድነት መመለስ ነው። ይህ ማለት ምዕራብ ትግራይ እና የተወሰኑ የራያ አካባቢዎች በመቀለው አስተዳደር ስር አልገቡም። ይህ የጊዜያዊ አስዳደሩ ውድቀት አይደለም። ምክንያቱ ግዛቶቹን መመለስ የነሱ ብቻ ስልጣን አይደለም። ለዚህ መፍትሄ መፈለግ የፌደራል መንግሥቱ ኃላፊነት ነው።” ይላሉ
ባለፈው ሳምንት ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም መዘግየቱ የገለጹ ሲሆን፤ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ዙርያ ከአማራ ክልል ባለስልጣናት ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ጉዳዩ በፌደራል መንግሥት እንዲፈታ ተወስኗል ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የአሸንዳ በአል ምክንያት በማድረግ በትግርኛ ባስተላልፉት መልዕክትም፣ ጦርነቱን ተከትሎ በምዕራብ ትግራይ እና ራያ የተቋቋሙ “ሕጋዊ ያልሆኑ” አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንደሚመለሱ መግለጻቸው ይታወሳል።
- አቶ ጌታቸው ረዳ በመግለጫቸው ያነሷቸው አምስት አንኳር ነጥቦች7 መስከረም 2023
- ለትግራይ የሚቀርበው እርዳታ መቋረጡን ተከትሎ 1 ሺህ 400 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ተነገረ18 ነሐሴ 2023
- የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም “ጉልህ ክፍተቶች” እንዳሉበት ተጠቆመ11 ሀምሌ 2023
ኃይሉ በበኩላቸው በክልሉ ከሰብዓዊ እርዳታም አቅርቦት ጋር በተያያዘም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በቂ ስራ አለመስራቱን ይናገራሉ።
“ሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ በማድረግ የተፈናቃዮች ሕይወት መታደግ አልቻለም።” በማለትም ይወቅሳሉ
በክልሉ መቅረብ የነበረበት እርዳታ ላይ ክፍተት በመኖር ረገድ በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ፕሮፌሰር ሸቲል ትሮንቮል ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ቢሆኑ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸውን ይጠቅሳል።
ፕሮፌሰሩ በክልሉ ለተቸገሩ ህዝቦች በእርዳታ መድረስ የፌደራል መንግሥት እና ሌሎች ድርሻ እንዳላቸው ያስረዳሉ።
“ከምግብ እስከ ሕክምና ቁሳቁስ የመሳሰሉት የሰብአዊ ድጋፎች ማስቀጠል ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስኬታማ አይደለም። ይህም ግን ለብቻው የሚፈጽመው አይደለም። ከፌደራል መንግሥት እና ዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት በጋራ የሚሰራ ነው። ይህ ለማሳካት የሁሉም ተሳትፎ የሚፈለግ በመሆኑ የተወሳሰበ ነው። “ ይላሉ።
በትግራይ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የተላከ እህል መዘረፉን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲሁምየአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ እርዳታ አቋርጠዋል።
ተቋማቱ በተቀረው ኢትዮጵያም ለተረጂዎች መድረስ የነበረበት መጠነ ሰፊ እርዳታ በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት አቀናባሪነት ስርቆት መፈጸሙን እና እርዳታውም ለኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት እና ለቀድሞ ተዋጊዎች መዋሉም ተነግሯል።
አለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች በትግራይ ክልል የሚያደርጉትን የምግብ እርዳታ ማቆማቸውንም ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በምግብ እጦት መሞታቸው ተገልጿል።
በትግራይ እርዳታን ላልተገባ ተግባር በማዋልና በስርቆት የተጠረጠሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች በተገነቡ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ አስተባባሪዎች እንዲሁም “የእርዳታ ምግብን የሚያከፋፍሉ አጋሮች” መሳተፋቸው ተገልጿል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም ተጠርጥረው ምርመራ እንደተከፈተባቸው የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የአደጋ ስጋት አስተዳደር መግለጹ ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ከእርዳታ እህል ስርቆት ጋር በተያያዘ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው በትግራይ ክልል የሚታየው የደህንነት እና የጸጥታ እጦት ፕሮፌሰር ሸቲል ትሮንቮል የሚያነሱት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ትልቁ ድክመት ነው።
“በትግራይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። በገጠር እና ትናንሽ ከተሞች ብቻ ሳይሆን መቀለን ጨምሮ በተደጋጋሚ እያየነው ነው። በቅርቡ በመቀለ የተገደለችው ዘውዱ የዚሁ ማረጋገጫ ናት። ለትግራይ ነዋሪዎች የደህንነት ከለላ መስጠት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቀጥታ ስልጣን ነው። በዚህ ረገድ ውድቀት አሳይቷል” ይላሉ።
ፕሮፌሰሩ የጠቀሷት ዘውዱ ሃፍቱ በመቀለ ከተማ አዲ ሓውሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሳምንታት በፊት በአንድ ምሽት እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏን ተከትሎ ለበርካቶች ቁጣ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ የክልሉ መንግሥት የማያውቃቸው የግል እስር ቤቶች እንዳሉ የገለጹ ሲሆን ኤርትራውያን ስደተኞች ጨምሮ ነዋሪዎች እየታገቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
“አጃቢዎች አሉን የምንል ሰዎች ጭምር አደጋ ውስጥ የማንወድቅበት ምክንያት የለም” በማለትም የችግሩን አሳሳቢነት በዚሁ ወቅት ገልጸው ነበር።
ቀደም ሲል ባስነበቡት ረጅም ጽሁፍ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመቀለ ብቻ የተወሰነ ነው በሚል የተቹት ፕሮፌሰር ትሮንቮል የጌታቸው ረዳ መንግሥት ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም እንቅፋቶች እየገጠሙት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
“በህወሓት ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ሕጉ እና በስልጣን ላይ የሚቆይበት ጊዜ በተመለከተ የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ እያየን ነው። ጌታቸውም በመግለጫው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከህወሓት ሰዎችም እንቅፋት እያጋጠመው እንደሆነ ጠቁሟል።“ ይላል
ከዚህ በተጨማሪ “በትግራይ ልሂቃን መካከል የስልጣን ሽኩቻ” በግልጽ እንደሚታይ የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፣ የጸጥታ አስከባሪው አካል ተጠሪነቱ ለአስተዳደሩ ብቻ አለመሆኑ ሁኔታዎችን ማባባሱን ያስረዳሉ።
ፕሬዝደንት ጌታቸው፣ አስተዳደራቸው በዞን እና ወረዳ ደረጃ የተቀባይነት ችግር እንዳጋጠመው እንዲሁም አስተዳደራቸውን ለማሳጣት የሚሰሩ አካላት እንዳሉ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የሳወት የውጭ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ኃይሉ ከበደ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም።
“በሕግ 60 በመቶ ስልጣን የወሰደው ህወሓት ነው። ጀነራሎቹ የህወሓት ደጋፊ ናቸው። የሲቪክ ማህበረሰብ እና ምሁራኑም ቢሆኑ ለህወሓት ያደላሉ። ስለዚህ በትግራይ ውስጥ ያለው የሽግግር መንግሥት መቶ በመቶ ህወሓት ነው” በማለት ከውስጥ እያጋጠመው ነው የተባለው እንቅፋት እውነት እንዳልሆነ ያብራራሉ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ደመወዝ አይከፍልም፤ ጡረታ አይከፍልም። ስለዚህ ‘ምን ሰራ’ ? ካላችሁኝመልሴ ‘ምንም’ ነው” የሚሉት ኃይሉ ከበደ በዚህ ረገድ የፌደራል መንግሥቱም በጀት ባለመልቀቁ ተጠያቂ እንደሆነ ይገልጻሉ።
“ጡረታ የሚከፍለው የፌደራል መንግሥት ነው። ጡረተኞቹ ምን አደረጉ? የመንግሥት ሰራተኞች ለምን ደመወዝ አይከፈላቸው። 100 ቢልዮን ለጦርነት ካወጣህ ለሰላም 10 ቢልዮን ማውጣት እንዴት ይከብዳል? “ በማለትም ይጠይቃሉ።
በጦርነቱ ምክንያት በጀት ተቋርጦባት በነበረው ትግራይ የአንድ ዓመት በጀት ብቻ እንደተፈቀደላቸው የገለጹት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በአሁኑ ሰአት ክልሉ የሚቀልባቸው 270 ሺህ ያልተሰናበቱ የትግራይ ኃይሎች አባላት በመኖራቸው ምክንያት፣ ለመንግሥት ሰራተኞች ደመመዝ ለመክፈል አስተዳደራቸው መቸገሩን ገልጸዋል።
የጌታቸው ረዳ መንግሥት፣ በአንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች የፌደራል መንግሥቱ ‘ምስለኔ’ እንደሆነ ሲገለጽ ይሰማል።
ፕሮፌሰር ትሮንቮል፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ እንዲሆን ተደርጎ መዋቀሩን ይገልጻሉ
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተዋቀረበት ህጋዊ አግባብ ብናይ፣ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ነው። ለትግራይ ሕዝብ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትግራይን ለማስተዳደር አስቸጋሪ ያደረገበት እሱ ነው። “ ይላሉ
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ሕዝብን ፍላጎት ለማንጸባረቅ የቻለውን ያህል እየሰራ ይመስለኛል” የሚሉት ትሮንቮል፣ በቀጣይ በክልሉ ውስጥ ያሉት ችግሮች ለመፍታት ከባድ ስራ እንደሚጠብቀው ይገልጻሉ።
ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚመራበት ብቁ እቅድ እንደሌለው የሚሞግቱት አቶ ኃይሉ ከበደ በበኩላቸው፣ ክልሉ በስርአት ለማንቀሳቀስ ፖለቲካዊ ለውጥ እንሚያስፈልግ ይናገራሉ።