
አምስት ፓርቲዎች ዛሬ ባወጡት ወቅታዊ መግለጫ በዘመነ ኢሕአዴግ ለተፈጠሩ ስህተቶች ሁሉ ይቅርታ ጠይቆ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሕዝብ እምነትና ተስፋ አምክኗል ሲሉ አስታወቁ።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ፣ እናት ፓርቲ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጋራ መግለጫቸው የመንግሥት ኃይሎች በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት የጅምላ ግድያና የድሮን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀዋል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አሁንም ብቸኛዉ መንገድ “ዉይይትና ድርድር” በመሆኑ መንግስት ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን በመወጣት የድርድር ጥያቄ እንዲያቀርብ፣ የመንግሥት ኃይሎች ከሰፈሩባቸዉ የመደበኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአስቸኳይ እንዲለቁ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም ባልታወቁ ሥፍራዎች በጅምላ ማጎሪያዎች የታሰሩ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ተዋጊ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ሕጎችንና ይህንኑ የሚደነግገውን የጄኔቫ ስምምነት እንዲጠብቁ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ጫና ማድረግ አለባቸው ሲሉ ፓርቲዎቹ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የብልፅግና ፓርቲ የመፍትሔ ሀሳቦች ቸል በማለት ችግሮችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት በሚያደርገው ሙከራ በሀገር ላይ ለሚደርሰው የከፋ ጉዳት በታሪክም፣ በሞራልም በሕግም ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል።
