አንባቢ

ቀን: September 24, 2023

በበቀለ ሹሜ

ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ አገሮች ጎራዊ ግጥሚያዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህ የዓለም ጦርነቶች ውስጥ የቀጥተኛ ግብግብ ሥፍራዎችና ተዋናዮች ቶሎ ሲበረክቱ ታይተው ነበር፡፡ አሁን ዓመት ገዳማ በሆነው አሜሪካና አውሮፓ ከሩሲያ ጋር በገጠሙት ጦርነት ይህ አልሆነም፡፡ በድብስብስ ዲፕሎማሲና በንግድ ከማገዝ በቀር የሩሲያ ባልንጀሮች በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ አልሆኑም፣ አሁን ድረስ የጦርነት ሜዳዋ ዩክሬን ነች፡፡ አሜሪካና አውሮፓ ጦርነታቸውን የሚያካሂዱት በጦር መሣሪያ አጋዥነት ተቆጥበው፣ የዩክሬንን ዜጎችና ውስን ቅጥረኞችን በተዋጊ ኃይልነት እየተጠቀሙ ነው፡፡

የጦርነቱ ተራዝሞ መቀጠል ከማንም በላይ ሩሲያን እንደሚያደቅ፣ የሩሲያ መድቀቅም የቻይና መድቀቅ መሆኑ ሁለቱ ሸሪክ ኃያላን (ቻይናና ሩሲያ) ዘግይቶ ታውቋቸዋል፡፡ ግን ጦርነቱን ለማስቆም የጠነከረ ሥራ እየሠሩ አይደሉም፡፡ ሁለቱም ወጥመድ ውስጥ የገቡ መስለዋል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ዓላማ ፈጣን የጦር ሜዳ ድል ሳይሆን ልዕለ ኃያላዊ አቅምን/አቅሞችን እየገዘገዙ የመዘረር ነው፡፡ የዩክሬን ጦር ሜዳነት ቶሎ እንዲያበቃ ፍላጎት የላቸውም፡፡ የጦር መሣሪያ አረዳዳቸው የረዥም ዕቅድ አመጣጠን ያለበት ነው፡፡ ሩሲያ ከዩክሬን ውጪ ሌሎች የኔቶ ቃል ኪዳን አገሮች ላይ እንድትተኩስም የትንኮሳ ግብዣ እየቀረበላት ነው፡፡ የፖላንድና የስሎቫኪያ የውጊያ አውሮፕላን ለዩክሬን መርዳት የቀድሞ ቂምን ያስታወሰ ትንኮሳ ነው፡፡ የፊላንድም ኔቶን መቀላቀል በረዥም ድንበር ኔቶ የሩሲያ ወሰንተኛ የሆነበት አዲስ ክስተት ነው፣ ‹‹ዩክሬይን ላይ ዘራፍ እንዳልክ ፊላንድ ላይ እስቲ እንይሃ!›› የሚል መልዕክትም አለበት፡፡

በኢንዶ ፓስፊክ እስያ በኩልም ጦርነት እንዲከፈት በተለይ አሜሪካ እየሠራች ነው፡፡ ቻይናን በቻይና ለመውጋት አገልግሎት ታይዋን ሌላ ዩክሬንነትን ታጭታለች፡፡ ፊሊፒንስ ከእነ ሕዝቧ የፀረ ቻይና – ሰሜን ኮሪያ የጦር ካምፕ መሆንን ፈቅዳለች፡፡ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያና አውስትራሊያ (አውከስ) ጥምረት ደግሞ ታይዋንና ፊሊፒንስን ከራስጌ አድርጎ አውስትራሊያን ዋና ጣቢያ ሊያደርግ ያቀደ ይመስላል፡፡ በዚህ ከበባ መሀል ውስጥ ያሉት ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ከአሜሪካ ጋር የጦር ልምምድ ቢያደርጉም፣ የአሜሪካ ጦርነት ንቁ አጋር በመሆን ረገድ ገና እንዳደቡ (ንቁ ተሳታፊነት የሚያስከትለውን ትርፍና ኪሳራ እየመረመሩ) ናቸው፡፡ ጃፓን የሩሲያ ነዳጅ አንዷ ሁነኛ ገዥ መሆኗም ይህንኑ ወዝወዝ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቻይና ትዕግሥቷ ተሟጦ ታይዋንን አኝ እንድትል ግፊቷን ማሞቅ ቀጥላለች፡፡

ሩሲያ ብዙ ኃይሎችን የገጠመችበት የአሁኑ ጦርነት በዚሁ ከቀጠለ የሩሲያ የጦርነት ‹‹ድሎች›› እዚያም እዚያም ቢታዩ እንኳ፣ እያንዳንዷ ቀን ለሩሲያ አቅም እያነሰ የሚሄድበት ነው፡፡ ለቻይናም እያንዳንዷ ቀን ብቻዋን ተጋልጣ የምትገኝበት ቀን መቅረብ ይሆናል፡፡ እነ ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች አጋሮቻቸው የሻንጋይ ትብብርንም ሆነ ሌሎች ሽርክናዎቻቸውን ከአዲሱ የሳዑዲ ዓረቢያና የኢራን ቅርበታቸው ጋር ሆነው፣ ምዕራብ አውሮፓን እንደ ምንም ወደ ሰላም እንዲመጣ የሚገፋ የእጥረት/የግሽበት ጭንቅ ውስጥ ካልከተቱት በቀር፣ አውሮፓና አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት ሊቀበሉት የሚችሉት ከጦርነት የመውጣት ‹‹መፍትሔ›› ሩሲያን አሸንፎ ከመቅጣት ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ ማለትም የተወሰዱ መሬቶችን መልሶ የዩክሬን ውድመትና የጦርነት ወጪ ካሳ ከማስተፋት ያነሰ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ ሩሲያ በተሸናፊነት ምርኮኛ ብትሆን የሚከተላትን የግዛት መበታተን ወዲያውኑ ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ተኩስ አቁሞና ከእነ አሜሪካና ዩክሬን ጋር ሰላም መፍጠር በአሁኑ ሰዓት የሁለት በኩል ፍላጎት መቻቻል የማይገኝበት ነው፡፡ እጅ ሰጥቶ የጦርነት ወጪን እጥፍ በእጥፍ ለማስመለስ የተራበ ጅብ የሩሲያ የተፈጥሮ ሀብት ላይ እንዲሰፍር ከመፍቀድ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡

ተኩስ አቁሞ ሰላም መፍጠር በአሁኑ ሰዓት እጅ እንደ መስጠት ያለ ወጥመድ የሆነባት ሩሲያ፣ ሄዳ ሄዳ ወደ ኑኩሌራዊ አጥፍቶ መጥፋት ዓይነት ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ ብትገባ ተጎጂነቱ የዓለም ይሆናል፡፡ ከኑኩሌር በመለስ በሆነ ጦርነት የትኛውም ጎራ ተቀናቃኙን ቢዘርር ደግሞ፣ ከማንም በላይ ደሃና ታዳጊ አገሮች እንደ ሰርከስ እንስሳት በአለንጋ ሾጥ እየተደረጉ ሁኑ የተባሉትን መሆን ዕጣቸው ይሆናል፡፡ ይህ ላይሆን የሚችለው ጦርነቱ ‹‹አሸናፊ››ንም ተሸናፊንም ካደከመና የኃያል ኃያልነት ክፍተት ከተፈጠረ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመሟላት ዕድሉ ጠባብ ነው፤ ምክንያቱም ከአሸናፊዎቹ ውስጥ እንደ ተሸናፊዎቹ የልዕለ ኃያልነት አቅሙ ዝሎ ቦታ የሚለቅ አሮጌ ቢኖርም ጉልበት ቆጥቦ ቦታ ለመረከብ ያደባ አይታጣምና፡፡

እናም የአሁኑ ሰዓት የአውሮፓና የአሜሪካ ፍላጎት በጦርነት ሩሲያን ማድቀቅ ነው የሚል ትንታኔ የሚሰጥበት ሳይሆን፣ የዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ተቋማትና የሲቪል ማኅበራት ኃይል አስተባብረው ለዓለም ሰላም የሚጮሁበት ነው፡፡ የቀደሙት ሁለት ‹‹የዓለም›› ጦርነቶች ገና ከፍጥጫቸው ጀምሮ የነቃ ተቃውሞ ነበረባቸው፡፡ ጦርነቱ ከዩክሬን ባሻገር በፓስፊክ እስያ ውስጥ ጦር ሜዳዎችን ከከፈተ በዚያ አካባቢ የተፈጠረ ብልፅግና ሁሉ ዶጋ አመድ ለመሆን ይጋለጣል፡፡ ኑክሌር ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ባይውል እንኳ ምድራችን በጥቅሉ ምን እንደሚተርፋት ለመናገርም ይቸግራል፡፡ እናም ቅጠል ጥለው እንደሚደነቁሩ ተክሎች ዛሬ በዝምታ መጋገር ናዳን ወይም ጎርፍን ተኝቶ ከመጠበቅ ብዙም አይርቅም፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ የዩክሬኑ ዘለንስኪ ይዋል ይደር እንጂ ድል የእኛ ነው ባይነት ነው፡፡ የሆነ መለኮታዊ ኃይል ገንዟት የኑክሌር አቅሟን ሳትጠቀምበት ሩሲያ ብትሸነፍ ዘለንስኪ ከተመለሱ መሬቶች ጋር ፍርስራሽ በፍርስራሽ የሆነች አገር ላይ ቆሞ በኩራት ‹‹ይኼው አሸናፊነታችን ዕውን ሆነ!›› ሊል ይሆን!

ነገዋ ያልለየላትን ዓለማችንን ዕጣ ለማቃናት የተከፈተ ልቦናና የጎበዘ ድምፅ ይስጠን!!

በዚህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ወደ ቤታችን አንዳንድ ጉዳዮች እንግባ፡፡

መሠረታዊ ዕሳቤዎች ከብሔርተኝነት ወደ ኅብራዊነት ለመሻገር

  1. ኢትዮጵያን ስንጠራ ወይም ስናስብ ምን ድቅን ይልብናል? ዝንጉርጉርነትና መወራረስ/ዓይነተ-ብዙነትና ድፍርስነት ገጽታዎቹ የሆነ አገር፡፡ በዓይነተኛ ማኅበረሰብነቱ ንፁህ የሆነ ማኅበረሰብ የለም፡፡ በእያንዳንዱ ማኅበረሰባችን የአመጣጥ ታሪክ ውስጥ ድፍርስነት አለ፡፡ ዛሬ ባለ ዓይነተኛነት ውስጥ ድፍርስነት አለ፡፡ ዓይነተኛ ማኅበረሰብ ከሌላ ማኅበረሰብ ባለው ጉርብትና ውስጥ የተቀላቀለ ድፍርስ አለ፡፡ ንፁህ ሶማሌ፣ ንፁህ ኦሮሞ፣ ንፁህ ጌዴኦ፣ ንፁህ ሲዳማ፣ ንፁህ ኮንሶ፣ ወዘተ የለም፡፡ ንፅህና ያለው ከየት እስከ የት ነው የሚል ነገር ውስጥ ብንገባ፣ ወይም የእያንዳንዱን ማኅበረሰብ ‹‹ትክክለኛ›› መለያ ወሰን ለመለየትና ለማስመር ብንባዝን ራስን አለማወቅ ይሆንብናል፣ ከእውነታ ጋር መላተም ይሆንብናል፡፡ ዓይነተኛነትን ከድፍርስነቱ (ከተወራራሽነቱ) ጋር መቀበል ይኖርብናል፡፡ ዓይነተኛነታችንን ከዝንጉርጉርነታችን ጋር አጣምዶ ማየት ማኅበረሰባችንንም አገራዊ ማንነታችንንም ማወቅ ነው፡፡ ስለዝንጉርጉርነት (ዳይቨርሲቲ) ሲወራ ብዙ ሰው ድቅን የሚልበት ኢትዮጵያ ብዙ ብሔረሰቦች የሚገማሸሩባት አገር መሆኗ ነው፡፡ ይህ አንድ ዓይና ግንዛቤ ነው፡፡ ግንዛቤያችን ሙሉ እንዲሆን ከፈለግን የየብሔረሰብ ጥንቅራችን ራሱ በዝንጉርጉርነት የተሞላ መሆኑን ማጤን አለብን፡፡ ሶማሌነት በዝንጉርጉርነት የተሞላ ነው፡፡ ኦሮሞነት ራሱ ዝንጉርጉር ነው፡፡ አማራነት ዝንጉርጉር ነው፡፡ አገውነት ዝንጉርጉር ነው፣ ወዘተ፣ ወዘተ…፡፡ ይህንን ለማስረዳት የመረጃ ችግር የለም፣ ጥልቅ ምርምር የሚሻም አይደለም፡፡
  2. ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅርና ኅብራዊ አመለካከት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር በማኅበር፣ በተቋም ወይም በፓርቲ ውስጥ ያለ ብሔረሰባዊ ስብጥርን (ዝንጉርጉነትን) የሚመለከት ነው፡፡ ‹ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር› በማለት ፈንታ ‹ዝንጉርጉር ጥንቅር› የሚል አባባል ከተጠቀምን ደግሞ ከብሔረሰብ ባሻገር በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሙያ፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ስላሉ ስብጥሮች ለማውራት ያስችለናል፡፡ ከየት ይምጣ ከየት ለማናውቀው ሰው ጉዳት ማዘን፣ አነሰም በዛ ሁላችንም ዘንድ አለ፡፡ ለአኅጉራዊ ወገንና ለአገር ልጅ መቆርቆርም እንዲሁ የትኛውም ሰው ዘንድ አለ፡፡ ግብታዊ ግንዛቤ መያዝና የጎለበተ ግንዛቤ መያዝ ግን ይለያያሉ፡፡ የሰው ልጅን ያለ አድልኦ የሚያገለግል ተቋምን የሥራ ተልዕኮ የሚቀበል ሰው ከጥላቻዎችና ለአገሬ/ለአኅጉሬ በየት በኩል ላድላ ከሚል አባዜ መላቀቅ ግዱ ነው፡፡ አኅጉራዊ ተልዕኮ ባለው ተቋም ውስጥ የሥራ ድርሻ የሚቀበልም ሰው ለአኅጉራዊ ማንነትና ዓላማ መታመን አለበት፡፡ በአገር ደረጃም እንዲሁ ከጎጥ/ከብሔረሰብ፣ ወዘተ ከለር መውጣት አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ለግንዛቤ እንዲረዳ የተጠቀምኩበትን የብርሃንን ኅብራዊ ባህርይ ልድገመው፡፡ ብርሃን ሁሉንም ከለር ብርሃኖች አካቶ ሲይዝ ከለር አልባ ነው፡፡ ከለር አልባው ብርሃን ሲሰተር (ሲተነተን) ግን የሁሉንም ከለር ብርሃኖች በሠልፍ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ እንደ ሰው፣ እንደ አኅጉር፣ እንደ አገር በማሰብና በመሥራትም ረገድ ከለር አልባ መሆን ማለት በየማዕቀፉ ውስጥ የሚገኙትን ከለሮች ሁሉ አካቶ ለአንዱም ሳያዳሉ ማስተዋል ማለት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ/ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ነን የምንል ሁሉ ይህን ባህርይ በማሟላት ረገድ ገና ገና ብዙ ይቀረናል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አገራዊ ነኝ የሚል ፓርቲ ኅብረተሰቧ የሚሻውንና የሚያሻውን (ሕይወትን የሚያራምድ) ሐሳብና ዕቅድ ማንገብ ይፈለግበታል፡፡ በጥንቅር ኢትዮጵያን መምሰል ይጠበቅበታል፡፡ ከለር አልባ መሆን ግዱ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ያለው በስመ ትግል ጠመንጃ ተኳሽ የተቃለለበትና የፌዴሬሽን አባል አካባቢዎች የአካባቢዬ የሚሉት ጦር የማያደራጁበት፣ ከመራራ ልምድ የተማረ የሰላም ሁኔታ፣ ሦስቱን ነገሮች በአግባቡ የያዙ ፓርቲዎች እየፈኩ እንዲወጡ የሚመች ነው፡፡ ‹‹የአማራ ክልል/የአማራ ሕዝብ›› የሚል አነጋገር ይዞ የማወራችሁ በአካባቢው ስላለው ስለአማራ፣ ቅማንት፣ አገውና ኦሮሞ ሁሉ ነውና እንደዚያ ተረዱኝ ማለት አይቻልም፡፡ አጠራርን ማረም ግድ ነው፡፡ በአካባቢያዊው የመንግሥት መዋቅር ውስጥም ዝንጉርጉርነት ሲገማሸር ማየት እንጠብቃለን፡፡ በየአካባቢው ማኅበረሰቦችን ያልዘነጋ ሁኔታ ውስጥ መግባት፣ የሁሉም ማኅበረሰብ ሰዎች በየአካባቢያቸው የሥራ ቋንቋ ሲምነሸነሹበትና ለየአካባቢያቸው ግስጋሴ ቤቴ/ወንዜ ብለው በንቃት አንድ ላይ ሲተምሙ ማየት አካባቢንም አገርንም ያጠነክራል፡፡

ድሮ ኢሕአፓ የሰሜን ሰዎች 80 በመቶ የሆኑበት የፓርቲ ጥንቅር ይዞ ሲዳሞ ውስጥ የትጥቅ ትግል ሊጀምር ሲያቅድ አንዱ ችግር፣ ‹‹ስለአማራ ገዥዎች/ባለርስቶች›› ጭቆና በሚወራበት ዘመን የአማርኛ አንደበት ይዞ የአማራ ገዥዎችን እንታገላለን ሊባል ነው? የሚል እንቆቅልሽ ገጥሞት እንደነበረ አንድ የኢሕአፓ ሰው በጻፈው መጽሐፍ ላይ አንብቤ ነበር፡፡ ዛሬ ካሉት ‹‹አገራዊ ነኝ›› ከሚሉ ፓርቲዎች ውስጥ ከብልፅግና ሌላ የጥንቅር ዝንጉርጉርነት በማሟላት ረገድ ተስፋ የሚደረግበት ኢዜማ ነው፡፡ ኢዜማ በሕዝብ ዘንድ የእኔ/የሁላችን ፓርቲ ለመባል ሁሉን የሚረታ ሐሳብ፣ ሁሉም አለሁበት የሚለው ዝንጉርጉርነት ላይ መድረሱና በከለር የለሽነት መታወቁ እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ የዚያን ቅርንጫፍ መሪ ኦሮሞ ማድረግ፣ ወይም ተሟሙቶ ኦሮሞ የሆኑ ቀስቃሾችና የምርጫ ዕጩዎች ማዘጋጀት በቂ አይሆንም፡፡ በኦሮሚያ አባላቱ ውስጥ ኦሮሞዎች ከሌሎች የማኅበረሰብ አባላት ጋር እንደ ልብ ሲገማሻሩ ለማየት ሲቻል ጭምር ነው ኢዜማ ኦሮሞም የእኛ ፓርቲ የሚለው መሆኑ የሚሳካለት፡፡ ከዚህ ግንዛቤ ሌሎች ‹‹አገር አቀፍ ፓርቲ›› ነን የሚሉም ትምህርት እንደሚያገኙ ይታመናል፡፡ ከተጠቀሰው መመዘኛ አኳያ፣ የብልፅግና ፓርቲና የኢፌዴሪ መንግሥት ወደፊት ሕዝብ አቀፍ ለውጥና ልማትን የሚያንቀሳቅሱ ከዋክብትን እንደሚያበራክት ይጠበቃል፡፡ ከፅንፈኝነትና ከጨለምተኝነት ጋር በተያያዘ የጦርነት ሁኔታ የዳሸቁት የሰሜን አካባቢዎች በቶሎ እስካልፈጠኑ ድረስም፣ ኢትዮጵያ ብዙ ከዋክብት የምታፈራበት አካባቢ ወደታች (እስከ ደቡባዊ ምዕራብና ምሥራቅ ድረስ) የተንሸራተተ ይመስላል፡፡

በዴሞክራሲ ውስጥ የመኖር ፍላጎትና እንጭጭነት

ሀ) በኢትዮጵያችን ውስጥ የዴሞክራሲ ግንባታ ገና መጀማመሩ ነው (ዴሞክራሲን መኖር የጀመርነው ገና የቅምሻ ያህል ነው)፡፡ ጅማሪውን የዴሞክራሲ ግንባታ እያፋፋን ለመሄድ የማንችልበት ሁኔታም ውስጥ ነበር የቆየነው፡፡ ይህ አባባል የነበርንበትን ፈተና በደንብ አይገልጸውም፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥታዊ ዓምዶች የተሰባበሩበትና የአንድ ክልል ገዥ ቡድን ክልሉን አገር ብሎና ‹‹መከላከያ ሠራዊት›› ገንብቶ አገርን የወረረበት ቀውስ ውስጥ ነበርን፡፡ አሁንም ይህ ቀውስ እንዳይደገም የታጠቀ ኃይል አደረጃጀት ሕጋዊ አስተዳደርን ገና በማስተካከል ላይ ነን፡፡ በአጭሩ የቆየነው አገራዊ የህልውና ግብግብ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ‹‹አገራዊ አርበኝነትን ከማጠናከር በስተቀር የሚረብሽና የሚያዳክም ማናቸውም የንግግርና የጽሑፍ ተግባር ሁሉ ያስጠይቃል›› የሚል አዋጅ ቢታወጅ ኖሮ እንኳ አግባብ እንጂ ጥፋት አይሆንም ነበር፡፡ ውድመቱ፣ ሽብሩ፣ ግድያው፣ ማፈናቀሉ፣ አሉባልታው፣ ሐሰተኛ ወሬው ፋታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ መረጃ አደራጅቶ ከሶ የመፋረድ መደበኛ ሒደት በጊዜው ኢትዮጵያ ከነበረችበት የፀጥታ ችግሮችና የዕርምጃዎች አጣዳፊነት ጋር የሚግባባ አልነበረም፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ አገር ወዳዶች በኅብረት የተዋደቁበት ታሪክ የፈካ ቢሆንም፣ ኃላፊነታቸውን ያላወቁ (ኢትዮጵያን እንወዳለን እያሉ የዞረባቸውም) ነበሩ፡፡

በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ዴሞክራሲን የመኖራችን ጉዳይ ገና በመቀማመስ ደረጃ መሆኑን የሳትን፣ ለዴሞክራሲ ያለ መዘጋጀት ቀርነት ያለብን፣ ዴሞክራሲን መኖር እንዴት እንደሆነ ያልገባን፣ ጋሪውና ፈረሱ በአግባቡ ባልተገናኙበት ሁኔታ ውስጥ በሠረገላ መንፈላሰስ የሚያምረንና በምዕራባያውያን ቤት ያየነው አይቅረን የምንል ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ እንገኛለን፡፡

ለ) እስካሁን ያልነውን ጠቅለል ብናደርገው፣ የዴሞክራሲ ጅምራችን የሰላም መናወጥ ገጥሞት የቆየ ብቻ ሳይሆን የኢዴሞክራሲና የፀረ ዴሞክራሲ ጭርንቁሶችም ያሉበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር በቤታችን ውስጥ ብዙ የሚጣሉ ነገሮች ገንቢነትም አፍራሽነትም፣ ወደፊት መሄድም ወደ ኋላ መሄድም፣ ሰላም በጥባጭነትም ሰላምን የመገንባት ጥረትም፣ ሕጋዊነትና ሕገወጥነትም፣ አምባገነናዊና ዘፈቀዳዊ ሥራዎችም፣ በሙሰኝነት/በአድሏዊነት መጠቃቀምና በሥራ/በችሎታ ማደግም በተበላለጠ ጥልቀትና ስፋት ይላፋሉ ማለታችን ነው፡፡

እነዚህን ነጥቦች የደረደርነው አራት ያህል ቁምነገሮችን ለማስጨበጥ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡