በአዲስ አበባ ከተማ የሞተር ብስክሌት፣ የባለ አራት እግር እና ባለሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ምሽት 12 ሰዓት አንስቶ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ መጣሉን የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው ለሞተር ብስክሌተኞች፣ የባለ አራት እግርና ባለሦስት እግር ባጃጅ አሽከርካሪዎች በሙሉ ባሰራጨው መልዕክት፤ ከዛሬ መስከረም 14/2016 ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ እስከ ማክሰኞ መስከረም 29/2016 እስከ ጠዋቱ 12:00 ድረስ ሞተር ብስክሌትን፣ የባለ አራት እግርና የባለሦስት እግር ባጃጅ ማሽከርከር ፍጹም የተከለከለ መሆኑን ነው የገለጸው።
ክልከላው የጸጥታ እና የትራፊክ ቁጥጥር የሚሰሩ አካላትን የማያካትት መሆኑንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ ባለንብረቶችም ሆኑ አሽከርካሪዎች እስከ ተጠቀሰው ቀን ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቁ የጠየቀ ሲሆን፤ “ይህንን በሚተላለፉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል።” ሲል አሳስቧል።
ቢሮው በተሽከርካሪዎቹ ላይ ክልከላውን ለምን እንደጣለ በግልፅ ያለው ነገር የለም።
