September 27, 2023 – Konjit Sitotaw
” ምዕመናን ከጠዋቱ 5 ሰዓት ጀምሮ ነጫጭ ልብስ በመልበስ ወደ በመስቀል አደባባይ መገኘት ይኖርባቸዋል ” – ቤተክርስቲያን
በመስቀል አደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሳውቃለች።
የደመራ በዓል አከባበር የቅድመ ዝግጅት ሥራን በተመለከተ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዛሬ ከቀትር ቀኋላ በመስቀል አደባባይ በመገኘት የቅድመ ዝግጅት ሥራው የደረሰበትን ደረጃ ተዛውረው የጎበኙ ሲሆን አጠቃላይ የዝግጅት ሥራው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ የክብር እንግዶች የሚቀመጡበትን የመቀመጫ መድረክ ከነ ሙሉ የድምፅ ግብዓቱ በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀት ትብብር ላደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን እና ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቅርበዋል።
የበዓሉን አከባበር ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት በዓሉን ለማክበር ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡ ምዕመናንም ከጠዋቱ 5 ሰዓት ጀምሮ ነጫጭ ልብስ በመልበስ ወደ በመስቀል አደባባይ መገኘት የሚኖርባቸው ሲሆን የመንግሥት የጸጥታ አካላት በዓሉን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማክበር ሲባል ለሚያደርጉት ፍተሻ ፍጹም ክርስቲያናዊ የሆነ ትብብር እንዲያደርጉ ቤተክርስቲያን አሳስባለች።
በአንዳንድ የመገናኛ አውታሮች የቤተክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት የሆኑ ከበሮ፣ ጸናጽልና መቋሚያ እንዳይገባ ተከልክሏል በማለት የሚናፈሰው ወሬም ፍጹም ሐሰት መሆኑን የገለፀችው ቅድስ ቤተክርስቲያን ” በዓሉን በትርኢት ለማክበር የተፈቀደላቸው ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ኤነዚሁኑ ኔዋያተ ቅድሳት ይዘው ይገኛሉ ” ብላለች።
በሌላ በኩል ፤ ወደ በዓሉ ማክበሪያ በሚደረግ ጉዞ ላይ በዓደባባዩ የሚገኙ የበዓሉ ታዳሚ ምዕመናን ያለምንም መግቢያ ባጅ ተፈትሸው ብቻ ወደ ዐደባባዩ መግባት የሚችሉ ሲሆን የመግቢያ ባጅ የሚጠየቁት የክብር እንግዶች፣ ጋዜጠኞችና ልዩልዩ የሚዲያ ተቋማት ብቻ መሆኑ ተገልጿል።
መረጃው የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው።
