September 28, 2023  – Konjit Sitotaw

ኢሰመጉ ዛሬ መስከረም 17/2016 ባወጣው መግለጫ  በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን  ጊዳ ወረዳ   ኤጀሬ ቀበሌ በቀን 02/01/16ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ  አባል የሆኑ 4 ሰዎች መገደላቸውን እና በኪራሙ ወረዳ  በቀን 02/01/16 የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው መቁሰሉን እንዲሁም በቀን 04/01/16 ወደ ጊዳ ከተማ  ይጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎችን የታጠቁ ኃይሎች መንገድ ላይ አዉርደው ወንዶችን በመለየት “ጋራ ዲቾ”(ዲቾ ዳገት) በሚባል ቦታ በርካታ ሰዎች መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን  በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን አንፍሎ ወረዳ  ሱዲ ቀበሌ  በቀን 27/12/15ዓ.ም  በመንግስት የጸጥታ አካላት በተፈጸመ ጥቃት  የሰው ህይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት መድረሱን  ኢሰመጉ ከአካባቢው ባገኘው መረጃ ለማወቅ  ችያለሁ ብሏል።

የኢሰመጉ ጥሪ፡
1,  የኦሮሚያ ክልል መንግስት በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ አካላትና በታጠቁ ኃይሎች በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲያስቆም፣
2, መንግስት  የዜጎቹን የሰብዓዊ መብቶች  የማስከበር ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣
3, የፌደራል እና የኦሮምያ ክልል መንግስታት በኦሮሚያ ክልል  የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች  በነጻነት ተንቀሳቅሰው የእለት ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ እና በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ዜጎችን የመጠበቅ ሀላፊነታቸውን  በአግባቡ እንዲወጡ፣

4, በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተደጋጋሚ በመንግስት የጸጥታ አካላት እና  የታጠቁ ኃይሎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ውስጥ እጃቸው ያለበትን አካላት መንግስት በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል
ብሏል ኢሰመጉ ፡፡