September 28, 2023 

የጉራጌ ህዝብ ከዚህ በላይ መገፋት እና መከዳት የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም “ጎጎት”

ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ  የጉራጌ ህዝብ ከዚህ በላይ መገፋት እና መከዳት የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም ሲል አስጠንቅቋል።

ጎጎት ይህን ያለው  የልዩ ወረዳዎች ምስረታና የወልቂጤ ከተማ ወሰን ማስከበርን  በተመለከተ መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው  መግለጫ ላይ ነው።

ፓርቲው በመግለጫው የጉራጌ ዞን ያለ ዞኑ ምክር ቤት ይሁንታና የህዝብ ፍቃድ  በክላስተር አደረጃጀት ተመስርቷል ያለውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን በብርቱ አውግዟል።

ምንም እንኳን ፓርቲው የክልሉን ምስረታ ከዚህ ቀደምም ሆነ በዚሁ መግለጫ ቢቃወምም በአዲሱ አደረጃጀት የተለያዩ የህግ ጥሰቶች እየተፈፀሙ መሆኑን አመልክቷል።

የአዲሱ ክልል ምስረታ እና ከምስረታው በኋላ የሚታዩ ጉዳዮች አዲሱ ክልል ጉራጌን ለማዳከም የተፈጠረ አደረጃጀት ነው የሚለው ህዝባዊ ስጋት የበለጠ የሚያጠናክር ሆኗል  ሲልም በይኖታል።

በመርሆ ደረጃ የተቀመጡ ጉዳዮች በአፈፃፀም ደረጃ በግልፅ እየተጣሱ ይገኛሉ  ሲል የሚወቅሰው ጎጎት  ከጉራጌ ዞን ወጥተው በራሳቸው ልዩ ወረዳዎች እንዲዋቀሩ በተደረጉ አደረጃጀቶች ውስጥ የጉራጌዎች መብት በግልፅ ተደፍጥጧል  ሲል ወንጅሏል።

ፓርቲው በመግለጫው በሁለተኛነት ያነሳው  የወልቂጤ ከተማ የወሰን ማስከበር የተመለከተውን ጉዳይ ነው።

የከተማዋ ህጋዊ ወሰን የማስከበር ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል ቆይቷል  የሚለው ጎጎት  በተለይም አጎራባች ወረዳዎች በዞኑ ስር የሚተዳደሩ ከመሆናቸው እና በተለይም ቀቤና እና አበሽጌ ወረዳዎች መቀመጫቸው ሳይቀር ወልቂጤ ከተማ አድርገው ሲሰሩ በመቆየታቸው ወሰን የማስከበሩ ስራ በእንዝላልነት ተይዞ ቆይቷል  ሲል ወቀሳን ባዘለ መልዕክት ጉዳዩን አስታውሷል።

ይህ መሆኑም  አንዱ አደረጃጀት በሌላው ወሰን ክልል ውስጥ እየገባ አልፎ አልፎ ግጭቶች ለመፈጠራቸው  ምክንያት ሆኗል ባይ ነው።

መግለጫውን በሦስት ገፆች የቀነበበው ጎጎት ቢደረጉ ያላቸውን አራት ምክረ ሃሳቦችን በመዘርዘር መግለጫውን ቋጭቷል።

በልዩ ወረዳዎቹ የተካለሉ ጉራጌዎች በአዳዲሶቹ አደረጃጀቶች ለመቀጠል፣ የራሳቸው አዲስ አደረጃጀት ለመፍጠር ወይም ከአጎራባች የጉራጌ ወረዳዎች ጋር ለመካለል ፍላጎታቸው በህዝበ ውሳኔ እንዲያረጋግጡ ህዝበ ውሳኔ እንዲደራጅላቸው  የጠየቀበት ቀዳሚው ምከረሃሳብ ነው።

በቀቤና ልዩ ወረዳ እና በወልቂጤ ከተማ መካከል በ1994 በተደረገው የድንበር ማካለል መሰረት የወሰን ማስከበር እና አስፈላጊ የመሬት ምልክቶች የማኖር ስራ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አስቸኳይ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ  ያለው የጎጎት መግለጫ  በመሆኑም ለአካባቢው ልማት እና ሰላም ሲባል ከቀቤና ልዩ ወረዳ ይፋዊ ምስረታ ጎን ለጎን የወልቂጤ ከተማ እና የልዩ ወረዳው ወሰን የማስከበር ስራ በአፋጣኝ እንዲካሄድ   ጠይቋል።

ፓርቲው በሦስተኛነት ባስቀመጠው ምክረሃሳብ  የጉራጌ ህዝብ ከዚህ በላይ መገፋት እና መከዳት የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም   በሚል ማስጠንቀቂያ ይጀምራል።

አከሎም  በመሆኑም አመራሩ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በጉራጌ ህዝብ ላይ ለዘመናት ያደረሰው በደል በሚክስ መልኩ በህዝባዊ ወገንተኝነት እና ተቆርቋሪን ስሜት እንዲንቀሳቀስ እና የጉራጌ ህዝብ መብት እንዲያስከብር   ጥሪ አቅርቧል።

የጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ መግለጫውን የቋጨው መንግስት የህዝቡን ጥያቄ እንዲያዳምጥና እንዲያከብር በመጠየቅ ነው።

መንግስት ለእነዚህ ህዝባዊ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ጎጎት መላውን የጉራጌ ህዝብ ያሳተፈ ሰላማዊ የመብት ትግል ንቅናቄ ለማድረግ የሚገደድ መሆኑን   በመጥቀስ ፓርቲው መግለጫውን ቋጭቷል።