September 29, 2023 – Konjit Sitotaw
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ አካላትና በታጠቁ ኃይሎች በንጹሃን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጠየቀ።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ትናንት ባወጣው መግለጫ መንግስት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ላሉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በቂ ትኩረት አለመስጠቱን ገልጿል።
ኢሰመጉ በመግለጫው እንዳመለከተው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ወረዳ ኤጀሬ ቀበሌ በቀን 02/01/16ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ 4 ሰዎች መገደላቸውን እና በኪራሙ ወረዳ በቀን 02/01/16 የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው መቁሰሉን ገልጿል።
እንዲሁም በቀን 04/01/16 ወደ ጊዳ ከተማ ይጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎችን የታጠቁ ኃይሎች መንገድ ላይ አዉርደው ወንዶችን በመለየት “ጋራ ዲቾ”(ዲቾ ዳገት) በሚባል ቦታ በርካታ ሰዎች መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አመልክቷል።
በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን አንፍሎ ወረዳ ሱዲ ቀበሌ በቀን 27/12/15ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ አካላት በተፈጸመ ጥቃት የሰው ህይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመጉ ከአካባቢው መረጃ ማግኘቱን ገልጿል።
ያም ሆኖ ኢሰመጉ ስለጉዳዩ መረጃ እንዲሰጠው የምስራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣የአስተዳደርና ጸጥታ እና የሚሊሻ ዘርፍ የጠየቀ ቢሆንም የቃል እንጅ የፅሁፍ ማረጋገጫ አለማግኘቱን አስታውቋል።
ስለሆነም በክልሉ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሰዎችን በሕይወት የመኖር እና የአካል ደህንነትን የመጠበቅ መብት የሚፃረር በመሆኑ፤ የፌደራል እና የኦሮምያ ክልል መንግስታት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ አካላትና በታጠቁ ኃይሎች በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ አካላትና በታጠቁ ሀይሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ዘርፈ ብዙ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እያስከተሉ በመሆናቸው መፍትሔ እንዲያገኙ በተከታታይ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በማውጣት የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ እንዲሰጡት ሲያሳስብ ቢቆይም ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ዜጎች ከፍተኛ ለሆነ የሰው ህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣የንብረት ዝርፊያና መውደም ፤ ለእገታና መፈናቀል እየተዳረጉ ይገኛሉ ሲል ኢሰመጉ በትናንቱ መግለጫው አመልክቷል።
