አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ኹኔታ እንዳሳሰባት ገለጸች
አርብ መስከረም 18 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አሜሪካ በኢትዮጵያ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ግጭት መባባስ እንዳሳሰባት በመግለጽ፤ ግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለትና በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈታ እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማት ሚለር አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በቢሯቸው በኩል ባወጡት መግለጫ፤ አንቶኒ ብሊንከን የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ችግሮችን ለመፍታት ዋነኛው መንገድ ሰላማዊ አማራጮችን መከተል ብቻ ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የፖለቲካ ውይይት እና ሰብአዊ መብትን ማክበር እንደሚገባ ማሳሰባቸውም ተመላክቷል።
በተጨማሪም በውይይታቸው የእርዳታ አቅርቦቱን ለማስጀመር የሚያስችል የተሻሻለ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ መነሳቱም ተነግሯል፡፡
ብሊንከን እውነተኛ፣ ታአማኒ እና ኹሉን አሳታፊ የሆነ የየሽግግር ፍትህን ለማስፈን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መግለጸቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።
በተመሳሳይ ሐምሌ 29/2015 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሃፊ አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ ሰላም፣ ብፅግናና መረጋጋት ላይ ያተኮረ የስልክ ውይይት ማድረጋቸው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።
በዚህም ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ማቆም ስምምነትን በመተግበር ረገድ መሻሻል መኖሩን ገልጸው የነበረ ሲሆን፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ኹኔታ ግን አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ ይህም ኹኔታ ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት ስጋት የሚፈጥር ነው ማለታቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
