ውሻው

ከ 4 ሰአት በፊት

ስሎቫኪያ ውስጥ በጉዞ ላይ ባለ መኪና ውስጥ በአሽከርካሪው ወንበር ላይ ውሻው ተቀምጦ ሲጓዝ በካሜራ የተቀረጸ የመኪና ባለቤት ቅጣት ተጣለበት።

በማኅበራዊ ሚዲያው ፌስቡክ ላይ የወጣ በተሽከርካሪዎች የፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራ የተነሳ ፎቶ እንደሚያሳየው ውሻው በሹፌሩ ወንበር ላይ ሆኖ መሪውን ተደግፎ ያሳያል።

የመኪናው ባለቤት ግን እያሽከረከረ ሳለ ውሻው ድንገት ዘሎ ጭኑ ላይ በመውጣቱ ነው ፎቶው ላይ ውሻው መሪውን ይዞ የታየው ሲል አስተባብሏል።

ነገር ግን ከስሎቫኪያ ዋና ከተማ ብራትስላቫ ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ስቴሩሲ በተባለችው ቦታ ያሉ የፖሊስ መኮንኖች ግን በአሽከርካሪው ምክንያት አይስማሙም።

እነሱ እንደሚሉት በፍጥነት መቆጣጠሪያው ካሜራ ላይ የተነሳው ምስል ምንም አይነት ድንገተኛ እንቅስቃሴን በመኪናው ውስጥ አያሳይም በማለት ቅጣት ጥለውበታል።

አስካሁን በውሻው ምክንያት በመኪናው ባለቤት ላይ የተጣለው ቅጣት በፍጥነት በማሽከርከር ወይም እየተጓዘ ባለ መኪና ውስጥ የቤት እንስሳን በአግባቡ ባለመያዝ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ፖሊስ አሽከርካሪዎች በመኪናቸው ውስጥ የቤት እንስሳትን ይዘው በሚጓዙበት ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል።

“በምታሽከረክሩበት ወቅት ትንንሽዬ እንስሳት ሳይቀሩ ሕይወታችሁን እና ጤናችሁን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ” ሲል ፖሊስ አሽከርካሪዎችን አስጠንቅቋል።