
ከ 7 ሰአት በፊት
ከተጀመረ ሦስት ሳምንታት ሊሆነው ለተቃረበው ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ የሆነው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ።
መንግሥት ለነዳጅ ምርቶች የሚሰጠውን ድጎማ ቀስ በቀስ ለማንሳት በያዘው ዕቅድ መሠረት የዓመቱን የመጀመሪያውን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ መደረጉን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አርብ መስከረም 18/2016 ዓ.ም. ምሽት አስታውቋል።
አሁን የተደረገው የዋጋ ማስተካከያ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከተደረገው ጭማሪ ጋር ሲነጻጸር በስፋት በሕዝቡ ዘንድ ጥቅም ላይ በሚውሉት የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ ላይ ከ41 ሳንቲም አስከ 3 ብር ከ41 ሳንቲም የሚደርስ ጭማሪ ተደርጓል።
በዚህም መሠረት በዋናነት ለትራንስፖርት አገልግሎት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው ቤንዚን ቀደም ሲል ከነበረው በሊትር የ74 ብር ከ85 ሳንቲም ዋጋ ወደ 77 ብር 65 ከፍ በማለት የ2 ብር ከ80 ሳንቲም ጭማሪ የተደረገበት ሲሆን፣ ነጭ ናፍጣ ከ76 ብር ከ34 ሳንቲም በሊትር ወደ 79 ብር ከ75 ሳንቲም ከፍ በማለት የ3 ብር ከ41 ሳንቲም ጭማሪ አሳይቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውለው በኬሮሲን ጋዝ ላይ ዝቅተኛ ጭማሪ የተደረገበት ሲሆን፣ በዚህም 76 ብር ከ34 ሳንቲም የነበረው ወደ 76 ብር ከ75 ሳንቲም ከፍ ብሎ የ41 ሳንቲም ጭማሪ ተደርጎበታል።
- የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ወይም እንዲቀንስ የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚወስነውስ ማን ነው?12 ጥቅምት 2022
- የነዳጅ ዋጋ መናር በጤናችን እና በከባቢ አየር ላይ የጋረጠው አደጋ30 ነሐሴ 2022
- የዋጋ ንረት ምንድን ነው? እንዴትስ ሊቀረፍ ይችላል?11 ሀምሌ 2022
ባለፈው ዓመት በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ጭማሪዎች በአገሪቱ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ መደረጉ ተዘግቧል።
በዚህም ከሰኔ 29/2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም. በነበሩት 14 ወራት ውስጥ በቤንዚን፣ በነጭ ናፍጣ እና በኬሮሲን ላይ 55 በመቶ እና ከዚያ በላይ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል።
መንግሥት ለረጅም ጊዜ ለነዳጅ ምርቶች ከፍተኛ መጠን የለው ድጎማን ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ ይህንን ለማስቀረት በሂደት የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ባወጣው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳለው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚኖረው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ለነዳጅ ሲደረግ የነበረውን ድጎማ ማስቀጠል እንዳልቻለ በመግለጽ ደረጃ በደረጃ ድጎማውን ሲያስቀር ቆይቷል።
በዓለም ገበያ ላይ ያለውን የነዳጅ ዋጋ መሠረት በማድረግ የሚወሰነው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ክለሳ በየወሩ የሚወሰን ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ባለበት እንዲቆይ ይደረጋል።
ባለፉት ጊዜያት የተደረጉት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪዎችን ተከትሎ በምርቶች እና በአገልግሎቶች ዋጋ ላይም ከፍተኛ ጭማሪ የተስተዋለ ሲሆን፣ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ባለው የአገሪቱ የኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ ጫናን መፍጠሩ ይነገራል።

