September 30, 2023 – Konjit Sitotaw 

” እውነቱን ለመናገር ነዋሪዎቹ እርቧቸዋል። እያለቀሱ ነው የተናገሩት። ድረሱልን እያሉ ነው ” – አቶ ምሕረት መላኩ

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በተለይም ሰሀላ ሰየምት ወረዳ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የወረርሽኝ ኬዞች እንዳሉ የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ ቢሮ ኃላፊ ኪዳት እድል (ዶ/ር) ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

ኪዳት (ዶ/ር) ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፣ ” ከድርቁ ጋር በተያያዘ መንገድ በእርግጥ አንድ አንድ የተቅማጥ ኬዞች አሉ ” ብለዋል።

አክለውም ፤ ” ነገር ግን ኬዙ አተት ወይም ኮሌራ ነዉ ብለን ለይተን ያስቀመጥነው ነገር የለም ከዚህ በኋላ ግን ከፍተኛ የሆነ ስጋት ነዉ ያለን በተቅማጥ በኩል የሚከሰት ወረርሽኝ ሊኖር ይችላል ” ብለዋል።

” ከድርቁ ጋር በተያያዘ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ሊጨምሩ ይችላሉ ” ያሉት ኪዳት (ዶ/)፣ ” ከምግብ እጥረቱ ጋር ተያይዞ በተለይ ከ 5 ዓመት በታች ባሉ ህፃናት የሳንባ በሽታ፣ ተቅማጥ እና ተያያዥ የሆኑ ለሞት የሚያደርሱ በሽታዎች ይከሰታሉ ” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

” እንዲሁም ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ተቅማጥ፣ ውሃ ወለድ የሆኑ በሽታዎች ይከሰታሉ ” ያሉት ኃላፊው፣ ” ከእንስሳት ጋር ተያይዞም የእንስሳት በሽታዎች ይከሰታሉ እነዚህ እንግዲህ ተያያዥ ችግሮች ናቸው ” ብለዋል።

” በወረርሽኝ መልክ ይከሰታሉ ብለን ከምናሰገባቸው በሽታዎች መካከል አንደኛው ወባ ሲሆን በተጨማሪም አተት የሚባለው በሽታ በተለምዶ ኮሌራ ድርቅ በተከሰተበት ወረዳ መከሰቱ የማይቀር ነው። እንዲያውም ቁጥር አንድ ይከሰታል ብለን ከምናስባቸዉ ወረዳዎች ሰሀላ ሰየምት ዋነኛው ነው ” ሲሉ አክለዋል።

የጤና መምሪያ ኃላፊው፣ ” እንደ ጤና ድርቅ ሲኖር የሚከሰቱ ብዙ ችግሮች አሉ ፊት ለፊት ያለው የረሀብ ችግር ነውና በተለይ አጥቢና ነፍሰጡር እናቶች ከ 5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት በጤና ጉዳይ ግንባር ቀደም ተጠቂ ናቸው ስለዚህ እሱ በጣም ትልቅ ችግር ስለሆነ የምግብ እጥረት ልየታ እያሰራን ነው ” ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር  የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋሰትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል የአማራ ክልል መንግሥት ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎች የዕለት ድጋፍ ለማድረስ ቢስማማም በጸጥታ ችግር መድረስ እንዳልቻለ ገልጸዋል።

ኃላፊው ከ1.2 ሚሊዮን በላይ እንስሳት ወደ አጎራባች ወረዳዎች ለመፈናቀል እንደተገደዱ በሰሀላ ሰየምት ወረዳ ሂደው ማረጋገጣቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

” ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቦታው ገብተው ድጋፍ በማድረግ ችግሩን እንስኪጋሩ ድረስ የክልሉ መንግሥት የዕለት ምግብ አቀርባለሁ ብሎ ውሳኔ አሳልፏል ” ያሉት አቶ ምህረት፣ ” ነገር ግን ሰሞኑን በጎንደር መስመር የጸጥታ ችግር ስለነበረ የትራንስፓርት ተጫራቾቹ ችግር አለ #አንሄድም አሉኝ ነው ያለው ” ብለዋል።

” መስከረም 18 እና ዛሬ መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም አንጻራዊ ሰላም ከሆነ ምግብ ይዘው እንዲገቡ ነው የተግባባነው ” ሲሉ አክለዋል።

እስካሁን የተገኘ ድጋፍ እንዳለና እንደሌለ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበላቸው ጥያቄም፣ ” የሕጻናት አድን ድርጅት (ሴቭዘቺልድረን) 475 ቤት መሪዎች ለእያንዳንዳቸው 21,000 ብር ድጋፍ አደርጋለሁ ብሎ ዛሬ መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም የተጠቃሚ ልየታ ሊጀመር ነው ” ብለዋል።

አክለውም፣ ” ቅድመ ዝግጅት ነውና እያደረግን ያለነው ወደ ሕዝቡ በተጨባጭ የገባ ድጋፍ ይለም ” ነው ያሉት።

ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበላቸው ጥያቄም፣ ” ነዋሪዎቹ እውነቱን ለመናገር እርቧቸዋል። እያለቀሱ ነው የተናገሩት። ድረሱልን እያሉ ነው ” ሲሉ ድርቅ በተከሰተበት አካባቢ በአካል ተገኝተው ያረጋገጡትን አስረድተዋል።

” እንስሳትንም ለማየት ሞክረን ነበር” ያሉት አቶ ምህረት የጋማ ከብቶች፣ የቀንድ ከብቶች፣ በግና ፍየሎችን ጨምሮ 1.2 ሚላዮን እንስሳት ሳር ወዳለባቸው አጎራባች ቦታዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ፣ ” ተከዜን ተሻግሮ በሚገኙ የሰሀላ ሰየምት 13 ቀበሌዎች ከአንዱም ቀበሌ ለእንስሳት የሚሆን መኖ አላገኘነም። የእንስሳት ሞት ቁጥርም እየጨመረ ነው” ብለዋል።

ቀይ መስቀል በአካባቢው ላይ ገብቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ እንዳቀረቡም አቶ ምህረት ገልጸዋል።