
1 ጥቅምት 2023, 08:09 EAT
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ጊዜያዊ በጀት እንዲጸድቅ በመጨረሻዋ ሰዓት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የመንግሥት ሥራ መዘጋትን አስቀረ።
ለአጭር ጊዜ የሚዘልቀው በጀት የፌደራሉ የመንግሥት ሥራዎችን እስከ ኅዳር አጋማሽ ይደግፋል ተብሏል።
ነገር ግን ይህ ለዩክሬን ምንም አይነት አዲስ ዕርዳታ ያላካተተው በጀት በሴኔቱ በ88 ድጋፍ እና በዘጠኝ ተቃውሞ ነው የጸደቀው።
በተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያላቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ጊዜያዊ በጀት የመጽደቁን ጉዳይ መቃወማቸውንም ተከትሎ ነው ለ45 ቀናት የሚዘልቀው የበጀት ሃሳብ በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ኬቨን ማካርቲ የቀረበው።
ነገር ግን ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በታየው አስደናቂ ለውጥ ሃሳቡን ሲቃወሙ የነበሩት ሪፐብሊካኖች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ለ45 ቀናት ክፍት እንዲሆኑ ያስቻላቸውን ለአጭር ጊዜ የሚዘልቀውን በጀት ድጋፍ ሰጥተውታል።
በጀቱ ከሪፐብሊካኖች በበለጠ በዲሞክራቶች ድጋፍ አግኝቷል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተሰጠው ቀነ ገደብ ትናንት እኩለ ሌሊት ከመጠናቀቁ ከደቂቃዎች በፊትም ነው አጽድቀው የፈረሙት።
ስምምነቱ ባይፈረም ኖሮ የመንግሥት ሥራዎች ይዘጉ ነበር የተባለ ሲሆን ይህም ማለት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፌደራል መንግሥት ሰራተኞችም ደመወዛቸው ይቋረጣል።
- የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለኢንቨስተሮች መሰጠቱን በመቃወም ሦስት ምሁራን ለጠ/ሚ ዐቢይ ደብዳቤ ጻፉ28 መስከረም 2023
- በኦሮሚያ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በታጠቁ ሃይሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ተጠየቀ29 መስከረም 2023
- በአየርላንድ የጂምናስቲክ ውድድር ተለይታ ሜዳሊያ ያልተሰጣት ጥቁር ታዳጊ ጉዳይ ውዝግብ አስነሳ29 መስከረም 2023
እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችም ይቋረጣሉ፣ ይገደባሉ ወይም ሰራተኞቻቸውን በመቀነሳቸው ከፍተኛ መጓተት ያጋጥማል። ትናንት እኩለ ሌሊትም ላይ ስምምነቱ በመጽደቁ የመንግሥት አገልግሎቶችን ከመቋረጥ አድኗቸዋል።
ስምምነቱ መጽደቁንም ተከትሎ የዲሞክራቱ የሴኔት የምክር ቤት መሪ ቹክ ሹመር “አሁን አሜሪካውያን በእፎይታ መተንፈስ ይችላሉ። አንዳንድ ሪፐብሊካኖች ሲገፉት የነበረው እጅግ አስከፊው፣ እና ጎጂው የበጀት ቅነሳ ቀርቷል” ሲሉም ተደምጠዋል።
በአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መዘጋት የሚያጋጥመው ሁለቱም ምክር ቤቶች አዲሱ የበጀት ዓመት ጥቅምት 1 ከመጀመሩ በፊት ባለው 30 በመቶ የፌደራሉ ወጪ ላይ መስማማት ሲሳናቸው ነው።
ሪፐብሊካኖቹ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ያላቸው ሲሆን የሴኔቱን የአመራር ሥፍራ የያዙት ደግሞ ዴሞክራት ሲሆኑ የትኛውም የገንዘብ ድጋፍ ከሁለቱም ወገኖች ስምምነት ያስፈልገዋል።
በባለፉት ሳምንታት በምክር ቤቱ ውስጥ የፌደራል ወጪዎችን ለማጽደቅ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም ከወግ አጥባቂ ሪፐብሊካኖች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞትም ነበር።
