
30 መስከረም 2023
በአሜሪካዋ የኒው ዮርክ ከተማ የተከሰተው ከባድ ውሽንፍ ድንገተኛ ጎርፍ በማስከተሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደነገገ።
የከተማው በርካታ የምድር ውስጥ የባቡር መስመሮች በጎርፍ የተሞሉ ሲሆን፣ የፍጥነት መንገዶችም በውሃ ተጥለቅልቀዋል። በዚህም ምክንያት በከተማዋ ካሉ አየር ማረፊያዎች መካከል ቢያንስ አንዱ ትናንት አርብ ተዘግቷል።
በከተማው አንዳንድ አከባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የጣለ ሲሆን፣ ትናንት ምሽት ዝቅተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሌሎችም ስፍራዎች ሊኖር እንደሚችል ተንበያ ተሰጥቷል።
የኒው ዮርክ ገዢ ካቲ ሆቹል “ይህ አደገኛ እና ለሕይወት የሚያሰጋ ውሽንፍር ነው” ብለዋል።
በኤክስ ወይም በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጨምረውም “በመላው ኒው ዮርክ፣ ሎንግ አይላንድ እና በሃድሰን ቫሊ አካባቢ በተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተደንግጓል” ብለዋል።
አገረ ገዢዋ ሰዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ ስፍራ እንዲቆዩ እና በጎርፍ በተሞሉ መንገዶች እንዳይጓዙም አሳስበዋል።
በጎርፉ ምክንያት እስካሁን ሞት ወይም ከፍተኛ ጉዳት አልተመዘገበም።
ከኒው ዮርክ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝው የኒው ጀርሲ ሆቦከን ከተማም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሏል።
የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አደምስ በበኩላቸው ሰዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ንቃት መቆየት ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
- የአሜሪካ ምስጢርን አሳልፎ ሰጥቷል ስለተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አስካሁን የምናውቀው30 መስከረም 2023
- በቱፓክ ሻኩር ግድያ የተጠረጠረ ግለሰብ ከ27 ዓመታት በኋላ ተይዞ ክስ ተመሠረተበት30 መስከረም 2023
- ተመራማሪዎች የስድስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለው የተባለ ጥንታዊ ጫማ አገኘን አሉ29 መስከረም 2023
ከንቲባው የከተማዋ የባቡር መስመሮች ከልክ በላይ እንደተጨናነቁ እና በከተማው ውስጥ መዘዋወር አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳምስ አርብ ምሽት በጎርፉ ምክንያት መውጫ ያጡ 15 ሰዎችን ከተሽከርካሪዎች እና ከምድር ላይ ከሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ክፍል ውስጥ መታደግ መቻሉን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የከተማው የትራንስፖርት ኤጀንሲ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ ከፍተኛ ጎርፍ የኒው ዮርክ ከተማ ዋነኛ የባቡር መስመሮችን በከፍተኛ ሁኔታ አስተጓጉሏል።
የተወሰኑ የምድር ውስጥ የባቡር መስመሮች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ በርካታ የባቡር ጣቢያዎች ዝግ ተደርገዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሕንፃዎች ውስጥ በጎርፍ መውጫ ያጡ ሰዎችን ለመታደግ ተንሳፋፊ ጀልባዎችን መጠቀማቸውም ተዘግቧል።
በርካታ አካባቢዎች ላይ ሰዎች በጎርፍ እስከጉለበታቸው ጠልቀው መውጫ በማጣት ግራ ሲጋቡ የሚያሳዩ ፎቶ እና ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ታይተዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራት አንዲት የከተማዋ ነዋሪ ከ25 እስከ 30 ሺህ ዶላር የሚገመት ንብረቷ በጎርፍ እንደወደመ ገልጻለች።
የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ በርካታ መንገዶች ዝግ እንደተደረጉ እና የአገሪቱ ብሔራዊ ዘብ መሰማራቱን ገልጿል።
ኒው ዮርክ ከተማ በዚህ ወር 14 ሺንች የሚለካ ዝናብ ያስተናገደ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 1882 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ እርጠበት አዘል የሆነ አየር ንበረት በመስከረም ወር ላይ ተመዝግቧል።
