September 30, 2023 – Konjit Sitotaw
በአፋር ክልል በአራት ወረዳዎች አሳሳቢ ድርቅ መከሰቱ ተገለጸ
በአፋር ክልል ዞን ኹለት ውስጥ በሚገኙ አራት ወረዳዎች አሳሳቢ ድርቅ መከሰቱን የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የአፋር ክልል የመንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሙሃመድ አሊ ቢኢዶ፤ በክልሉ በብዛት አርብቶ አደሮች ባሉበት እና ከትግራይ ክልል ጋር አጎራባች በሆኑ ምስራቃዊ አፋር አካባቢዎች በክረምቱ ወቅት መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቅ መከሰቱን ገልጸው፤ በዚህም በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የክልሉ የግብርና ባለሙያ በበኩላቸው፤ በዞን ኹለት ውስጥ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ ከ3 ሺሕ 500 ሄክታር በላይ ሰብል ወድሟል ብለዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም በአብኣላ፣ ብርሃሌ፣ ደሎል እና ቆነባ በተባሉ አራት ወረዳዎች ዝናብ የዘነበው በሚያዚያ እና ግንቦት ወር ብቻ መሆኑን ጠቁመው፤ “አርሶ አደሮች ዝናብ ይዘንባል በሚል ተስፋ የእርሻ ማሳቸውን በቆሎ እና ማሽላ የዘሩ ቢሆንም፣ ዝናቡ ሳይዘንብ በመቅረቱ ከ200 ሄክታር መሬት በላይ ሰብል ተዘርቶ ሳበቅል ቀርቷል።” ነው ያሉት።
በአራቱ ወረዳዎች በዝናብ እጥረት ታረሶ ያልተዘራ ከአንድ ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ የእርሻ መሬት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ ከነሐሴ 04 እስከ ነሐሴ 10/2015 ድረስ ተከስቶ በነበረው የአንበጣ መንጋ በአብአላ ወረዳ ብቻ ከ480 ሄክታር መሬት በላይ ሰብል መውደሙንም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በብዛት የሚያመርቱት የበቆሎ እና የማሽላ ሰብል ቢሆንም፤ በአንበጣ መንጋ እና በድርቁ ምክንያት ሰብላቸው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ነዋሪዎች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡
በሰው እና በእስንሳት ላይ የደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ምን ያህል እንሆነ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመውም፤ በክልሉም ይሁን በፌደራል መንግሥት በኩል እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልተደረገ ገልጸዋል።
በድርቁ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች አንዳንድ በጎ ፈቃደኞች በቤተክርስቲያን እና በመሰጂድ ገንዘብ በማሰባሰብ እንዲሰጣቸው እያደረጉ ቢሆንም፤ “ይህ በቂ ባለመሆኑ ችግሩ ሳይባባስ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል።” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአፋር ክልል ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ በትግራይ ክልል 27 ወረዳዎች እንዲሁም በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በተከሰተው አስከፊ ድርቅ የሰዎች ሕይወት እያለፈ ይገኛል።
