የተደረመሰው ቤተ ክርስቲያን

ከ 3 ሰአት በፊት

በሜክሲኮ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ጣር መደርመሱን ተከትሎ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን እና 20 ሰዎች ደግሞ መውጫ ማጣታቸው ተዘግቧል።

በሜክሲኮ ሲውሳድ ማደሬ ከተማ የሚገኘው የሳንታ ክሩዝ ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ መውደቁን ተከትሎ 49 ሰዎች በደረሰባቸው ጉዳት ሆስፒታል መወሰዳቸውንም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኝበት የባህር ዳርቻ ግዛት የሆነው ታሙሊፓስ ፖሊስ አደጋው በደረሰበት ወቀት 100 የሚሆኑ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰባስበው እንደነበር ገልጸዋል።

በወቅቱ የጥምቀት አገልግሎት እየተሰጠ እንደነበረ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በፍርስራሽ ውስጥ መውጫ ካጡት መካከል በርካታ ህጻናት እንደሚገኙ የሚታመን ሲሆን እነሱን ለመታደግ እየተደረገ ያለው ጥረት ቀጥሏል።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሰዎች በፈረሰው ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ተሰባስበው በተስፋ መቁረጥ ፍርስራሽ ውስጥ የቀሩ ሰዎችን ሲፈልጉ ታይተዋል።

ሰዎች ፍርስራሹን ለማስወገድ አካፋና ዶማ ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መሄዳቸው ተነግሯል።

ሆኖም ከጊዜ በኃላ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጋሩ ምስሎች ትላንት ከሰዓት ወደ ፈረሰው ቤተ ክርስቲያን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተው ታይተዋል።

በነዚሁ ገጾች በፍርስራሾች ውስጥ በህይወት ያሉ ሰዎችን ለመታደግ የህክምናና የነፍስ አደን ቁሶች እንዲቀርብ ጥሪ ተላልፏል።

ባለስልጣናት ፍራስራሹ ባለበት ቦታ ጸጥታ እንዲሰፍን ጠይቃል። ይህም ፍርስራሽ ውስጥ የቀሩ ሰዎችን የእርዳታ ድምጽ ለመስማት ያግዛል ብለዋል።

የታምፒኮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጆዜ አርማሲ አልቬሬዝ ካኖ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በፍርስራሽ ውስጥ የቀሩትን ለመታደግ የነፍስ አድን ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጨምረውም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ካሉ በኃላ “እግዚአብሄር ይርዳችሁ” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።