October 2, 2023 – Konjit Sitotaw
ኢዜማ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ መታሰርን እንደሚደግፍ መግለጫ አወጣ። ካሁን ቀደም ግለሰቡ ሲያዙ ስብሰባ ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ብርሃኑ ነጋ እንዲያዘ ለአብይ አገዛዝ ባስተላለፈው መልዕክት መሰረት እንደሆነ ከውስጥ ምንጮች የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ጫኔ ከበደን ጽንፈኛ አማራ ነው ብሎ ያሳፈነው ብርሀኑ ነጋ ነው! ተብሎ መፃፉ ይታወሳል። በተባለው መሰረት ይህንን የሚያጠናክርና የሚያረጋገጥ መግለጫ ከኢዜማ ተሰጥቷል።

አንድ የኢዜማ ውስጥ አዋቂ በውስጥ መስመር በላከልኝ መልዕክት የኢዜማው ጫኔ ከበደ በዐቢይ አሕመድ ደኅንነቶች የታፈነው ንጹሐን ዘመዶቹ ፋኖን ትደግፋላችኹ ተብለው በደብረ ማርቆስ ከተማ ከሰሞኑ ስለተገደሉበትና መከላከያ ፋኖን ሳይኾን ሰላማዊ ሰዎችን ከቤታቸው እያወጣና በየመንገዱ እያሳደደ ያለ ፍርድ በጭካኔ እንደሚረሽን በግፍ የተረሸኑ ዘመዶቹን እንደ አብነት በኢዜማ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ አቅርቦ ዝም ማለት የለብንም በማለቱ እንደሆነ ገልጾልኛል።
ጫኔ ከበደ በኢዜማ የአመራር መድረክ ይህንን ከተናገረ በኋላ የብርሀኑ ነጋ መልስ በድርጅታችን ውስጥ ያሉ የአማራ ጽንፈኞችን መንግሥት አይታገስም የሚል እንደነበረና ጫኔ ከበደንም ያሳፈነው ብርሀኑ ነጋ ራሱ መሆኑን በውስጥ መስመር በላከው መልዕክት ገልጦልኛል።
ውስጥ አዋቂው የኢዜማ ሰው አክሎም የጫኔ ከበደን መታሰር ተከትሎ ኢዜማ “እስሩን” በመቃወም ያወጣው መግለጫም ሊቀመንበሩ ታስሮ ድርጅቱ ዝም አለ እንዳይባል የይምሰል መኾኑን ጫኔ በተናገረበት መድረክ እዚያው ነበርኹ ያለው የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ አባል በመልዕክቱ አውስቷል። ሲል አቻምየለህ ታምሩ መጻፉ ይታወሳል።
የኢዜማ መግለጫ ከዚህ በታች ይመልከቱት
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም የፓርቲያችን ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋልን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ጉዳዩን በጥንቃቄና በትኩረት እንደሚከታተለው፣ መረጃዎችንም በተከታታይ እንደሚያሳውቅ መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት የፓርቲያችን ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይህንኑ ጉዳይ እንዲከታተል የሰየመው ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በቁጥጥር ስር የዋሉት በፓርቲያችን ባላቸው ኃላፊነት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ መሆኑን መረጃዎች አግኝተናል፡፡
ይህ መረጃ ከተገኘ በኋላ የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ተወያይቷል።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን ሰቅዞ የያዘው የፖለቲካ ውጥረት መነሻ በሁለት እሳቤዎች መካከል በሚደረግ ፅንፍ የረገጠ መካረር መሆኑ እሙን ነው፡፡ በአንድ በኩል በእውቀት፣ እውነት፣ መርኅ እና ምክንያታዊነት ምሶሶዎች ላይ የተመሠረተው የዜግነት ፓለቲካ፤ ከዚህ በተለየ ደግሞ ተበደልኩ፣ ተገለልኩ፣ የሚገባኝን ያህል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የፖለቲካ ውክልና ተነፍጎኛል . . . ባህሌን፣ ቋንቋዬን እና ወግ ሥርዓቴን ማሳደግ አልቻልኩም በሚሉ በዘውግ ላይ በተንጠለጠለ ልዩነትን መሰረት ባደረገ የማንነት ፖለቲካ መካከል ሲደረግ የቆየው ግብግብ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው ብለን እናምናለን።
በሁለቱ የፖለቲካ መስመሮች መካከል የሚደረገው ትንቅንቅ የሚያስከትለውን የሕይወት እና የንብረት ውድመት፣ በአጠቃላይ ህዝባችንን ከችጋር እና ጉስቁልና በሚያላቅቅ የልማት ሥራ ላይ መዋል ያለበት ውስን የሀገር ሃብት ብክነትን በማስቀረት ከትጥቅ ትግል ይልቅ በመተማመን ላይ የተመሠረተ የሃሳብ ትግል (በሰላማዊ ንግግር ችግሮችን መፍታትን ልንከተለው የሚገባ ብቸኛ የትግል ስልት) እንደሆነ የሚያሳይ አቋማችንን ደግመን ደጋግመን የገለፅነው የአደባባይ ሃቅ ነው።
ኢዜማ በመርኅም ሆነ በተግባር በዜግነት የፖለቲካ አስተሳሰብ እና በፀና የሰላማዊ ትግል መስመር የሚያምን፣ ይህንኑ መርኅ ብቻ ተከትሎ የሚሠራ፣ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ በዘውግ ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሆነ በኃይል መንግሥታዊ ሥልጣን ለመያዝ በሚደረግ ትግል ውስጥ ፈጽሞ የማይሳተፍ ብቻ ሳይሆን በዚህ መንገድ ተጉዘን ዕረፍት ለናፈቀው ህዝባችን የሰላም አየር ልናመጣለትም ሆነ በዘላቂነት ወደተረጋጋ የፓለቲካ ሥርዓት ልንደርስ እንደማንችል ያለጥርጥር የሚያምን ድርጅት ነው፡፡
ኢዜማ ከሰላማዊ የትግል ስልት ውጪ በዘውጌ ብሔርተኝነትም ሆነ አፈሙዝ በታከለበት የትግል መንገድ መንቀሳቀስን ድርጅቱ የቆመበትን መርኅ መቃረን አድርጎ ያየዋል።
ማንኛውም የኢዜማ አባል ብሎም ከወረዳ እስከ ብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ድረስ የሚሳተፍ አመራር ከዚህ የድርጅቱ ፅኑ ዕምነት ውጭ የተንቀሳቀሰ እንደሆነ ድርጅቱን ለማፍረስ እንደሚሰራ ተደርጎ እንደሚቆጠር መታወቅ አለበት። ኢዜማ ውስጥ የማይነካም ሆነ የማይተካ አባልም ሆነ አመራር የለም! ስለሆነም ከድርጅቱ ዓላማ እና የትግል መስመር ባፈነገጠ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አባላቱ ላይ የፀና አቋም ይይዛል።
ኢዜማዊነት በምንም መንገድ ሁለት የማይታረቁ ሃሳቦችን እያጣቀሱ መሄድን የማይፈቀድ እንደሆነ መላው የድርጅታችን አባላት፤ እንደዚሁም በክብር፣ በነፃነት እና በእኩልነት የመኖር ዋስትና እንዲረጋገጥለት ዘወትር የምንታገልለት መላው የኢትዮጰያ ህዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን።
ሀገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ደረጃ በደረጃ ልትላቀቅ የምትችለው በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ የምንሳተፍ ኃይሎች (መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኋን፣ . . . እና መላው የሀገራችን ዜጎች) ሕጋዊ እና ሰላማዊ የሆነ ትግልን በመከተል እና ከዛ ውጪ ያለ አማራጭ የትግል መስመር ውስጥ ባለመሳተፍ እና ባለመደገፍ እንደሆነ እናምናለን። በተለይ በአሁኑ ሰዓት የሀገራችንን መሠረታዊ ችግሮችን ሥርዓት ለማስያዝ እንደሃገር ብዙ ተስፋ የሰነቅንበት ሀገራዊ ምክክር ሊጀምር በመሆኑ ትኩረታችን እሱ ላይ መሆን አለበት ብለን በጽኑ እናምናለን።
የሃገራዊ ምክክሩን ውጥኖች ተግባራዊነት በማረጋገጥ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚያዝበት ብቸኛው መንገድ እንዲሆን እና ከዛ ውጪ ያሉት አማራጮች በኢትዮጵያ ምድር የማይሞከሩ ብቻ ሳይሆኑ የማይታሰቡም ጭምር እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን።
በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የሚገኙ አባላት እና ደጋፊዎች ከመርሐችን እና በግልጽ ካስቀመጥነው የሰላማዊ ትግል አቅጣጫችን በተለየ መንገድ መጓዝ የፓርቲውን ሕገ ደንብ በግልፅ መጣስ ከመሆኑም በላይ ከዘመን ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ የሀገራችንን የፖለቲካ ችግሮቻችንም ሆነ ህዝባችንን አንገት ያስደፉ እና ለከፋ ድህነት እና ጉስቁልና የዳረጉ ስብራቶቻችንን በማባባስ ሂደት ላይ ከመሳተፍ ተለይቶ አይታይም።
ኢዜማውያን ይህን በውል በመገንዘብ ከሰላማዊ ትግል እና ከዜግነት ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጭ ያለን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መደገፍ፣ የሀሳብም ሆነ የተግባር ተሳትፎም ሆነ ትብብር ማድረግ ከኢዜማዊነት መርኅ ማፈንገጥ መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
የፓርቲያችን ሊቀመንበር ጉዳይም ከዚህ ከላይ ከተገለፀው መርኅ አንጻር የሚታይ ይሆናል ሲል ፓርቲያችን ይገልፃል።
መስከረም 21/2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
