
ከ 54 ደቂቃዎች በፊት
ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ ኬንያ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ነው የተባለ የመረጃ መረብ ጥቃት እንዳጋጠማት የአገሪቱ የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ተቆጣጣሪ አካል አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ እንዳለው አንድ ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ 860 ሚሊዮን የመረጃ መረብ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ የጥቃቶቹ “ድግግሞሽ፣ ረቂቅነት እና በመረጃ ደኅንነት ላይ የደቀኑት ስጋት መጠን” በኬንያ ወሳኝ የመረጃ መረብ መሠረተ ልማቶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አመልክቷል።
በአውሮፓውያኑ 2017 ኬንያ 7.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የመረጃ መረብ ጥቃቶች አጋጥመዋት ነበር።
- ኬንያ በሄይቲ ሥርዓተ አልበኝነትን ለመቆጣጠር ፖሊሶቿን ለማሰማራት ከተመድ ፍቃድ አገኘችከ 9 ሰአት በፊት
- ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ተፈጸመበትከ 3 ሰአት በፊት
- የዛሬ 10 ዓመት በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የደረሰው የላምፔዱዛው እልቂት3 ጥቅምት 2023
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ሩሲያ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የበይነ መረብ ሰርሳሪ ቡድን “አኖኒመስ ሱዳን” እንደፈጸመው በተነገረው የመረጃ መረብ ጥቃት በአገሪቱ ወሳኝ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎሉ አድርጎ ነበር።
ይህም ቪዛ፣ ፓስፖርት እና የመንጃ ፈቃድ ለማግኘት እና ለማደስ የሚያስፈልገው ማመልከቻን ጨምሮ በአገሪቱ አምስት ሺህ የሚደርሱ የበይነ መረብ ወሳኝ የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲቋረጡ አድርጓል።
የበይነ መረብ ጥቃቱ በተጨማሪም በኢንተርኔት አማካይነት የባቡር ትኬት ለመቁረጥ የሚያስችለውን ሥርዓት እንዲሁም በሞባይል ገንዘብ የማዘዋወር አገልግሎትን እንዳይሠራ አድርጎት ነበር።
የኬንያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን እንዳለው ባለፉት 12 ወራት በአገሪቱ ውስጥ ከተመዘገቡት የመረጃ መረብ ጥቃቶች ውስጥ 79 በመቶ የሚሆኑት የበይነ መረብ ወንጀለኞች ወደ ተቋማቱ የኮምፒውተር ሥርዓቶች ዘልቀው በመግባት የፈጸሙት ነው።
እንዲሁም ከጥቃቶቹ 14 በመቶው በአደገኛ ሶፍትዌሮች አማካይነት፣ 6.5 በመቶው የበይነ መረብ ወንጀለኞች ኢላማ የሆኑትን ሰርቨሮች በመረጃ በማጥለቅለቅ በመሠረተ ልማቶቻቸው ላይ ጫና እንዲፈጠር በማድረግ ሲሆን፣ የቀሩት ደግሞ የበይነ መረብ መተግበሪያዎችን ኢላማ ያደረጉ ናቸው።
ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣኑ እንዳለው ኬንያ በበይነ መረብ ወንጀለኞች ኢላማ በመደረግ ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል በአፍሪካ አህጉር ሦስተኛ አገር ነች።
