
2 ጥቅምት 2023
በግብጽ የፖሊስ ህንጻ ላይ በተቀሰቀሰ ከፍተኛ የእሳት አደጋ ቢያንስ 38 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት እና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ኢስማኢሊያ በምትገኘው ከተማ የሚገኘው ተቋም ላይ የተነሳውን ቃጠሎ የእሳት አደጋ ሰራተኞች መቆጣጠር ችለዋል ተብሏል። እንዲሁም የአካባቢው ሆስፒታሎችም በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።
ህንጻው በእሳት መያያዙንም በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
በፖሊስ ህንጻው ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ እንዲጣራ ትዕዛዝ መተላለፉንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በቃጠሎው የጸጥታ ዳይሬክቶሬት ዋና መስሪያ ቤት አንዳንድ ክፍሎች መውደሙንም የመከላከያ የሲቪል ምንጮች ገልጸዋል።
የግብጽ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 50 አምቡላንሶች እና ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ ህንጻው የላከ ሲሆን ቢያንስ 24 ሰዎች ከመተንፈሻ ችግር በተያያዘ እና ሁለቱ ደግሞ በቃጠሎ ምክንያት ህክምና ተደርጎላቸዋል።
- በሜክሲኮ የቤተ ክርስቲያን ጣራ ተደርምሶ 7 ሰዎች ሲሞቱ 20 ሰዎች መውጫ ማጣታቸው ተነገረ2 ጥቅምት 2023
- ለ1977ቱ የኢትዮጵያ ረሃብ እርዳታ ማሰባሰቢያ የነበረው ሙዚቃ ወደ መድረክ ሊመጣ ነው2 ጥቅምት 2023
- እስራኤል ውስጥ በኤርትራውያን መካከል በተፈጠረ አምባጓሮ አንድ ሰው ሲገደል በርካቶች ቆሰሉ2 ጥቅምት 2023
ቃጠሎው ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል እና የሰው ህይወት አልፎም ሊሆን እንደሚችል አንድ ግብጻዊ ጋዜጠኛ ዘግቧል።
ሮይተርስ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር በመጀመሪያ ሲታገሉ የነበረ ሲሆን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው እሳቱ ከሶስት ሰዓታት በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
በግብጽ ውስጥ የእሳት አደጋ መከላከያ ደንቦች እምብዛም ስለማይተገበሩ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ምላሾች ከመዘግየታቸው ጋር ተያይዞ የእሳት አደጋዎች ይከሰታሉ።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በካይሮ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የ41 ሰዎች ህይወት አልፏል።
