October 4, 2023 

በኢትዮጵያ በተደረጉ ግጭቶች የተፈጸሙ አሰቃቂ ወንጀሎችን የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ማስረጃ መገኘቱ ተገለጸ

 ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ምርመራ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር እና ሌሎች ክልሎች በተደረጉ ግጭቶች የተፈጸሙ አሰቃቂ ወንጀሎችን የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ማስረጃ መገኘቱን የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ አሁን ባለው የክልሎች አለመረጋጋት እንዲሁም በፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ፤ አገሪቱ በቀጣይ ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጋላጭ የመሆን “ከፍተኛ አደጋ” ተጋርጦባታል ሲል ገልጿል፡፡

በሪፖርቱ በአሁኑ ሰዓት የሚስተዋለው ኹከት፣ አለመረጋጋት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በአገር አቀፍ ደረጃ እና በመላ ንኡስ ዞኖች የሚፈጸም መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይም ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

ወደፊት ለሚፈጸሙ አሰቃቂ ወንጀሎች ስጋት፤ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ምርመራ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች መግለጻቸውም ተነግሯል፡፡

በአማራ ክልል በፋኖ እና በፌደራል መንግሥቱ መሀል የተፈጠረው ግጭት የልዩ ሃይል ትጥቅ መፍታት ጋር በተያያዘ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ በየጊዜው የተለያየ ሪፖርት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚደርሱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለማምጣት የሚጥረውን ለውጥ እና አንድነት በተደጋጋሚ የሚፈጠረው አለመረጋጋት እንዳይሳካ ማድረጉም ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ። በዚህም አገሪቷ ለበለጠ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጋላጭ መሆኗ እየተነገረ ያገኛል፡፡
___
አዲስ ማለዳ