October 4, 2023 – Konjit Sitotaw
በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከ640 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ እንቅፋት ሆኗል ተባለ
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅና ግጭት ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ከ640 ሺሕ በላይ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ፤ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ እንቅፋት ሆኖብኛል ሲል የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ፤ “በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ለተለዩ ከ640 ሺሕ በላይ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተን ሥራ የጀመርን ቢሆንም፤ በክልሉ ያለው የጸጥታ ኹኔታ እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “በክልሉ በሰሜን ጎንደር ዞን፣ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ በማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እና በአንዳንድ የወሎ አካባቢዎች አሳሳቢ ድርቅ በመከሰቱ ነዋሪዎች አስቸኳይ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡” ብለዋል፡፡
እንዲሁም በድርቅ አማካኝነት ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጭ ተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጭቶች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችም አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የምግብ ግብዓቶችን በትራንስፖርት ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ እንዳልተቻለ ገልጸው፤ “የክልሉ የጸጥታ ኹኔታ በአጭር ጊዜ መፍትሔ ካላገኘ፤ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡” ብለዋል፡፡
“ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች የሚሆነውን የምግብ ቁሳቁስ በወረታ እና ኮምቦልቻ በሚገኙ መጋዝኖች ለማጠራቀምና ወደ ተለያዩ ቦታዎች ለማከፋፈል ጥረት እያደረግን ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
ለአብነት በሰሜን ጎንደር በተከሰተው ድርቅ 452 ሺሕ ዜጎች መጎዳታቸውንና 202 ሺሕ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ወቅት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የተሰበሰበው የምግብ ቁሳቁስ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚሆን ቢሆንም፤ እሱንም በአግባቡ ለተጎጂዎች ማድረስ አልተቻልም ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በድርቁ ሳቢያ ዜጎች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ በመሆኑ ኹሉም አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ ገልጸው፤ መንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም አጋር አካላት የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያቀርቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
