October 4, 2023 

በመዲናዋ ከ244 በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች የመስሪያ ቦታችን በመፍረሱ ለከፋ ችግር ተዳርገናል አሉ

 (አዲስ ማለዳ) በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ በአምስት የንግድ ማህበራት ተደራጅተው የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ከስድስት ወራት በፊት እንሰራበት የነበረው ቦታ በመፍረሱና “ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል” ቢባልም እስከአሁን፤ ስላልተሰጠን ለከፋ ችግር ተዳርገናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማህበሩ አባል፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኙ 244 በላይ ከሚሆኑ አካል ጉዳተኞች መሃል ለአምስት ግለሰቦች ብቻ የሥራ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን፤ እነሱም ቢሆን ሥራ አለመጀመራቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች የተቀሩት 239 የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች በሙሉ ከሥራ ዉጪ መሆናቸውን ገልጸው፤ አብዛኛዎቹ ወደ ልመና እንዲሁም ወደተለያዩ ክፍለ አገራት መሄዳቸውን አመላክተዋል።

ክፍለ ከተማው ከዚህ ቀደም ምትክ ቦታ ሊሰጥ እንደነበረ ገልጸው፤ ነገር ግን ቦታው የወንዝ ዳርቻ ከመሆኑ ባሻገር ለአካል ጉዳተኛ አመቺ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩ “እኛ የምንጠይቃቸውን ቦታ ሊያመቻቹልን ፍቃደኛ አይደሉም” ሲሉም ተደምጠዋል።

በተጨማሪም ይሰሩበት የነበረው ስፍራ አሁን የመኪና ማቆሚያ እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሆኖ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

“ይሄንንም ክፍለ ከተማውን በምንጠይቅበት ሰዓት፤ ደንብ አስከባሪ የተባሉ ኃይሎችን እየላኩ ከቦታው ያስነሷቸዋል የተረሳ ሲመስላቸው ደግሞ ይመለሳሉ፡፡” ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም “ክፍለ ከተማው የኛን ቦታ ለሌሎች ለመስጠት የማደራጀት ሂደት ላይ መሆኑንም ሰምተናል፡፡” ብለዋል።

የማህበሩ አባል አክለውም፤ “የአዲስ አበባን ዉብ እና ጽዱ የማድረግ እቅዱን በምንም መልኩ አንቃረንም፣ ነገር ግን አካል ጉዳተኛው ብቻ ተነጥሎ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው የፈረሰብን፡፡” ብለዋል።

እንዲሁም የሥራ ቦታዎች ላይ የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች ማን እንደወሰዳቸውና የት እንዳሉ እንደማያውቁ በመግለጽ፤ “ወደ ስፍራው ስናቀናም በመንግሥት ኃይሎች ድብደባ ወከባ ይደርስብናል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በዚያው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ሌሎች ወረዳዎች ላይ አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ሰዎች አሁንም እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ የእነሱ ብቻ ተነጥሎ የፈረሰበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።

እንዲሁም ሌላ የማህበሩ አባል ስምንት ቤተሰቦችን እንደሚያስተዳድሩ በመግለጽ፤ ለስድስት ወራት ሥራ ፈትተው በመቀመጣቸው ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር እንደተሳናቸው የተናገሩ ሲሆን፤ ቀድሞ ይሰሩበት የነበረውን ቦታ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ውስጥ የሚሰራ ሰው እያከራየው መሆኑንም ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሥራ ዕድል ፈጠራ መምሪያ ኃላፊ እመቤት ተስፋዬን ያነጋገረች ቢሆንም፤ “በአሁኑ ሰዓት ሌሎች ወቅታዊ ሥራዎች አሉን” በማለታቸው ምላሻቸውን ለማካተት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።