
5 ጥቅምት 2023
በአውስትራሊያ ከ120 በላይ የሚሆኑ ኢንዶኔዥያውያን ታዳጊዎች እንደ አዋቂ ታስረዋል በሚል በመንግሥት ላይ በቀረበው ክስ አሸናፊ ሆነው ካሳ እንዲከፈላቸው ተወሰነ።
የአውስትራሊያ መንግሥት ለእስር ለተዳረጉት እንዲሁም ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ናችሁ በሚል ክስ ለቀረበባቸው ታዳጊዎች 17 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።
12 ዓመት ያልሞላቸው ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ታዳጊዎች በእስር ላይ እንደነበሩም ተመልክቷል።
አውስትራሊያ ካላት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሚመለከት ፖሊሲዎች ጋር በተያያዘ ተከታታይ ክሶች እየቀረቡ ባለበትም ወቅት ነው እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰው።
“በውጤቱ በጣም ተደስተናል። ይህንን ከጀመርን አስር ዓመታት አልፈዋል” ሲሉ ከታዳጊዎቹ ጠበቆች አንዱ ሳም ቲየርኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአውስትራሊያ መንግሥት ላይ ክስ ያቀረቡት አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በጀልባ ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2009 እና 2012 መካከል ለእስር ተዳርገዋል።
ታዳጊዎቹ ታስረው የነበረው በክሪስማስ እና በዳርዊን ደሴቶች ላይ እንደሆነም ተነግሯል።
ታዳጊዎቹ በጀልባዎቹ በመሳፈር ወደ አውስትራሊያ ያቀኑት ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፈልበት ሥራ እንደሚያገኙ እንዲሁም አንዳንዶቹ መድረሻቸውን ሳያውቁ በአዘዋዋሪዎች ተታለው ነው ተብሏል።
- በምሥራቅ ኢትዮጵያ ጎርፍ ሊወስደው የነበረን ሕጻን ለማዳን የተፈጸመ ሰብአዊነት እና ጀግንነት5 ጥቅምት 2023
- ለኢትዮጵያ የተቋቋመው የተመድ መርማሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታ ሳይራዘም መቅረቱ ወቀሳ ቀረበበት5 ጥቅምት 2023
- አሜሪካ ከኢራን የያዘችውን 1.1 ሚሊዮን ጥይቶች ለዩክሬን ሰጠች5 ጥቅምት 2023
በአውስትራሊያ ሕግ መሠረት በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡት ታዳጊዎች ወደ መጡበት ሊመለሱ ይገባ ነበር።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አገሪቷ ባስቀረችው ኤክስሬይ ምርመራ አማካይነት ባለሥልጣናቱ ታዳጊዎቹ ከ18 ዓመት በላይ እንደሆኑ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል ተብሏል።
ጉዳዩን ይፋ በማድረግ እና እንዲጣራ ከረዱት መካከል የእስር ቤት ጠባቂዎች አንዱ ኮሊን ሲንገር ነው።
ጠባቂው በአውሮፓውያኑ 2018 ለቢቢሲ እንደተናገረው የአውስትራሊያ መንግሥት “ሕጻናቱን ዕድሜያቸውን አውቆ ሆን ብሎ እንዳሰራቸው” አጋልጧል።
የኢንዶኔዥያ መንግሥትም ታዳጊዎቹን ለመርዳት “ምንም ማድረግ አልፈለገም” ሲልም ጠባቂው ተናግሮ ነበር።
የአውስትራሊያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የታዳጊዎቹ መብቶች እንደተጣሱ እና ጉዳያቸውም በስህተት ተይዞ እንደነበር በሪፖርቱ አውጥቷል።
በመንግሥት ላይ ክስ ካቀረቡት አንዱ የሆነው አሊ ጃስሚን በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ የአውስትራሊያ ባለሥልጣናትን በቸልተኝነት እና በዘር መድልዎ ከሷቸዋል።
