October 7, 2023 

ተረኛነት ክንፍ አውጥቶ ሲበር! አባዱላ ገመዳን በምሳሌነት፤ ( አንዳርጋቸው ፅጌ)

በኢትዮጵያ ውስጥ ተረኛነት ዳዴ ማለቱን በቀናት፣ መራመዱን በወራት ጨርሶ፣ አሁን ክንፍ አውጥቶ እየበረረ ነው። ተረኛነት በባህርይው ከጥቂቶች ጋር ብቻ የሚተሳሰር ነው። የፖለቲካ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ በእጃቸው ካስገቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ደሃ በመሆኗ በተለይ የኢኮኖሚያዊ ተረኛነት ህዝባዊ መሆን አይችልም። የፖለቲካ ተረኛነትም እንደዚሁ። ቁልፍ የሆኑ ስልጣኖች ውሱን ስለሆኑ። ነገር ግን ማህበራዊና ስነልቦናዊ ተረኛነቶች በስሜት የሚገለጹ ስለሆነ ሁሉንም ህዝብ ባይሆንም ስፋት ያለውን ማህበረሰብ ሊበክሉት ይችላሉ።

ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ዘራፊዎቹ በዋንኛነት ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። እነዚህ የትግራይ ተወላጆች በአንደኛ ደረጃ ይቀመጡ እንጂ ብቻቸውን ሳይሆን ከሌሎች ብሄር ተወላጆች ጋር ነበር የሚዘርፉት። ሆኖም ግን በሂደት እንዳየነው ብዙ ጊዜ የሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ዘራፊነት ጎልቶ አይሰማም። የሌሎች ብሄር ተወላጆች ዘራፊነት ከወያኔ ዘራፊዎች እኩል ጎልቶ እንዲሰማ ባለማድረጌ ይቅርታ ጠይቄያለሁ። መዘዙን እያየነው ስለሆነ።

ማህበራዊና ስነልቦናዊ የተረኛነት ስሜት ከቀጥተኛ ተጠቃሚነት ጋር አይተሳሰርም። ተረኛ ከሆነው ልሂቅ ጋር ቋንቋ እና ባህል በመጋራት ብቻ የሚመጣ ስሜት ነው። ጥናት አልተደረገበትም እንጂ እንዲህ አይነት ስሜት በገጠር መኖሩ አጠያያቂ ነው። በገጠር ብዙው ሰው የሚኖረው ከራሱ ዘር ጋር ስለሆነ። ሆኖም ግን የተረኛነት ስሜት በከተሞች ትናንት በወያኔ ጊዜ ነበር ዛሬም በኦህዴድ ዘመን አለ። ፍርፋሪ ያላገኘው ሁሉ በተረኛነት ስሜት ሲወጠር ይታያል። ሌላው ህዝብ የጥቂቶችን ዘራፊነት የአንድ ብሄር ህዝብ ተረኛነት እንደሆነ አድርጎ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ የሚያደርገውም ይህ እውነታ ነው። አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ የሚለው ተረት ሁኔታዎችን በደንብ ገላጭ የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው።

የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘራፊዎች ነበሩ። እንደ ኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች ባይሆኑም። ዝርፊያቸው ግን እንኳን የትግራይን ህዝብ አይደለም የአብዛኛውን የወያኔ አባላትን ተጠቃሚ ያደረገ አልነበረም። አሁንም የኦህዴድ ተረኛነት፣ በረሃብ ሲያልቅ የነበረውን ወደፊትም ሊያልቅ የሚችለውን የቦረና ኦሮሞ ወይም የኦነግ ሸኔ ደጋፊ እየተባለ የሚጨፈጨውን ኦሮሞ ወይም እንደሌሎች ብሄሮች እህትና ወንድሞቹ በስራ አጥነትና በኑሮ ውድነት የሚጠበሰውን ሰፊና ደሃ ኦሮሞ አይወክልም። እንዲህም ሆኖ የኦሮሞ ተረኛነት የሚል ቋንቋ የሌሎች ህዝቦች ቋንቋ ሆኗል። ባዶ ሆዱን በተረኛነት ሞልቶ የሚናውዘው በመብዛቱ።

ከላይ እንደ መንደርደሪያ ያቀረብኩት “ህዝብ ተረኛ ሆኖ አያወቅም፤ በስሙ ስልጣን የያዙ ግን እንዲያ ሆኖ እንዲታይላቸው ይተጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ብቻቸውን ርቃናቸውን ቆመው እንዳይታዩ ነው። ገመናቸውን በህዝብ መሸፈን ይፈልጋሉ።” ለማለት ነው። ስለተረኛነት ሳነሳ ጥቂት ሌቦችን እንጂ አንድን ህዝብ የሚመለከት እንዳልሆነ ለማመላከት ነው። ይህ ማብራሪያ በቅርስነት እንዲቀመጥ እንጂ፣ ተረኞቹ ይህን ማብራሪያ ተመልክተው የማህበራዊ ሚድያ ቅጥረኛ ተናካሽ ውሾቻቸውን “ህዝብ ሰደበ ብላችሁ ንከሱት” ብለው ጃስ እንደሚሏቸው ጠፍቶኝ አይደለም።

ከዚህ ቀደም እደገለጽኩት ተረኛነት ግለሰቦችን ምሳሌ አድርጎ የሚገለጽ በመሆኑ ነው፣ ግለሰቦችን የማነሳው። ፈርዶበት፣ ዛሬ አባዱላ ገመዳን የማነሳው ሌላ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የተረኛነት ምሳሌ ሆኖ ስላገኘሁት ብቻ ነው። የግል ጠብ የለኝም።

በወያኔ ዘመን የመጀመሪያው የራሱን ቤት ያሰራ ጄነራል አባዱላ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሌሎቹ ጓዶቹ ገና ሌብነት ውስጥ ስላልገቡ “ከየት አምጥተህ ሰራህ?” የሚል የግምገማ ጥያቄ አንስተውበት ነበር። አባዱላም “ቫርኔሮ በነጻ ሰራልኝ፣ የመከላከያ መኪናዎችና ቁሳቁሶች ተጠቅሚያለሁ ወዘተ” በማለት መልስ ከሰጠ በኋላ የግምገማ ኪኒኑን መዋጡን ሰምቻለሁ። ከኪራይ ከሚያገኘው ገቢ ላይም የሆነ ውሳኔ ተወስኖበት ነበር። ያ የግምገማ ምክንያት የሆነ ህንጻ፣ በወቅቱ 15ሽህ ብር የሚከራይ ቤት ነበር። ከዛ በኋላ እነዛ ገምጋሚዎች ግማሽ ሚሊዮን ብር በወር የሚከራይ ቤት ሰርተው አርፈውታል። የያኔው ያኔ ነው ወደ ዛሬው እንመለስ።

አባዱላ ገመዳ ምንም እንከን የማይወጣለት አላማ ያለው በልጁ በዲቦራ ስም የበጎ አድራጎት ስራ የሚሰራ ፋውንዴሽን እንዳቆመ ይታወቃል። ከፍተኛ የሚድያ ሽፋን አግኝቶ ስለነበር።

ፋውንዴሽኑ ነጮች ዳውን ሲንድሮም በሚሉት ህጻናትን የአካልና የአይምሮ ዘገምተኛ በሚያደርግ የተፈጥሮ ችግር ዙሪያ በተጠቁት ላይ የሚሰራ ነው። ፋውንዴሽኑ ለእነዚህ ህጻናት የተለየ እንክብካቤ ለማድረግ የተቋቋመ ነው። ይህ የሚበረታታ ነው። በአባዱላ ታዋቂነት የተነሳ መንግስት፣ የሃገር ውስጥ ባላሃብቶች እና የውጭ መንግስታት ማንም ማግኘት የማይችለውን ማበረታቻ አድርገውለታል። ሁሉም የአገር ውስጥ ሚድያዎችም ዜናው ዘግበውታል።

ወደተረኛነት አጀንዳችን የሚወስደን ከእነዚህ ማበረታቻዎች አንዱ በሆነው ለአባዱላ ለፋውንዴሽኑ ህንጻ መገንቢያ ከተሰጠው መሬት ጋር የተያያዘው ነው።

ሲጀመር ፋውንዴሽን በፍትሃብሄር ህግ እንጂ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅት አዋጅ መቋቋም አይችልም። መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለቤቱ ህዝብ ነው። ፋውንዴሽን ግን የግል ነው። ስለዚህም ፋዎንዴሽን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች መንግስት የሜሰጣቸውን ድጋፍ ማግኘት አይችልም። ፋዎንዴሽኖች የሚመሰረቱት በመስራቾቹ ሃብት እንጂ በመንግስት በሚሰጥ ሃብት አይደለም። ሆኖም ግን ወያኔዎች ኤፈርትን ፋውንዴሽን ብለው በግል ንብረነት አስመዝግበው፣ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መብት አጎናጽፈው ሲዘርፉ እንደነበር ይታወቃል። ከጦርነቱ በኋላ ኤፈርት ወደትግራይ ህዝብ ንብረትነት ዞሮ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በመሆን የህግ ቅራኔው ይቃለል የሚል እምነት ነበረን። አልሆነም።

ይህ ያልሆነው የኦሮሞ ብልጽግና ተረኞች እንደወያኔ በፋውንደሽን ስም ድርጅት እያቆሙ የመንግስት ሃብት መዝረፍ ስለፈለጉ ነው። የኣባዱላ ፋውንዴሽን እንዲህ አይነቱን ዘረፋ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። በምስሉ ላይ ከተቀመጡት ደብዳቤዎች መረዳት እንደሚቻለው የአባዱላ የዲቦራ ፋውንዴሽን እንደ መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ተቋም ተቆጥሮ 2148 ካሬ ሜትር ቦታ ከሊዝ ክፍያ ነጻ በሆነ ውል ተሰጥቶታል። አንዳንድ ሰዎች እንኳን በአእምሮ ዘገምተኝነት ለሚሰቃዩ ዜጎቻቻን አገልግሎት የሚውል ቀርቶ፣ መሬት ለማንም ሌባ ይታደል የለም ወይ ይሉ ይሆናል። እውነት ነው መሬቱ ለተባለለት አላማ ውሎ ቢሆን ኖሮ እኔም በቸልታ ባለፍኩት ነበር። በሚቀጥሉት መስመሮች እንደሚታየው ይህ አልሆነም። በመሆኑም የአብዱላን ስም የምናነሳው መሬት ህገወጥ በሆነ መንገድም ቢሆን ለበጎ አላማ በማግኘቱ ሳይሆን ያገኘውን መሬት እንዳሻው እንዲያደርገው የተሰጠው ፈቃድ ከተረኛነት ጋር ስለሚያያዝ ነው። ተረኛነት የወለደውን ማን አለብኝነትና ህገ ወጥነት ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳይ ነው።

በምስሉ ላይ የምትመለከቱት የመሬት ካርታና ደብዳቤ እንደሚያሳየው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8፣ ሚያዚያ 5 2013 ቀን፣ 2148 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ከሊዝ ነጻ የሆነ ቦታ “የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸውን ዜጎች ለመርዳታ የሚያስችል የግንባታ ቦታ” በሚል ምክንያት ለአባዱላ ድርጅት ለዲቦራ ፋውንዴሽን ተሰጥቷል። ፋውንዴሸ የግል ድርጅት ስለሆነ ለአባዱላ ተሰጥቶታል ማለት ነው። ስብሃት ነጋ የኤፈርት ፋውንዴሽን ሃብት የትግራይ ህዝብ ሳይሆን የኛ ነው እንዳለው ማለት ነው። ቀደም ብለን እንደገለጽነው ይህ በራሱ ህገወጥ ድርጊት ነው። እሱን እያወቅን ቀጥሎ ወደተፈጸመው ድርጊት እናምራ። በምስሉ ላይ የምታዮት በ04 12 2015 የተጻፈ ደብዳቤ የሚቀጥሉትን ከተረኛነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ድርጊት ሲፈጽም ይገኛል።

በዚህኛው ደብዳቤ በመጀመሪያው ደብዳቤ ላይ ስለቦታው አገልግሎት በሚለው ስፍራ ላይ ያልሰፈረ “ቦታው ለገቢ ማስገኛ የሚሆን ለቅይጥ አገልግሎት” የተሰጠ የሚል ሃተታ ተካቶበታል። የግል ንብረት የሆነው ፋውንዴሽን በማን አለብኝነት መንግስታዊ ያለሆነ ድርጅት ተደርጎ ስለተወሰደ ይህ ችግር አልነበረውም። ምክንያቱም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተሰጣቸው መሬት ላይ ህንጻ ገንብተው ኪራይ እየሰበሰቡ የበጎ አድራጎት ስራቸውን ማካሄድ ስለሚችሉ። ቀጥሎ ደብዳቤው ላይ የሰፈረውን ስናነብ ነው በመጀመሪያው መሬት ሲሰጥ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ያልነበረ ነገር ለምን መግባት እንዳስፈለገ የሚገባን።

ይህ ደብዳቤ ዲቦራ ፋውንዴሽን በራሱ መሬቱን ለማልማት የሚጠይቀውን ከፍተኛ ወጪ መሸፈን ስለማይችል ከተባባሪ አልሚ ጋር ለመስራት እንደተገደደ ይገልጻል። እዚህም ላይም አልሚው ከዲቦራ ፋውንዴሽን ጋር አንድ አይነት ውል ተዋውሎ በደብዳቤው የሰፈረውን ከሃያ ፎቅ በላይ ርዝመት የሚኖረውን፣ የመኖሪያን የንግድ ቤቶች ህንጻ ለዲያቦራ ቢያስረክብ ምንም ችግር የለውም። ዲቦራ የመኖሪያና የንግድ ቤቶቹን እያከራዬ ከፊሉን እዳ መክፈያ ከፊሉን የድርጅቱን ወርሃዊ ወጪዎች መሸፈኛ ሊያደርግ ይችላል።

ደብዳቤው በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጠው ቁም ነገር፣ ዲቦራ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን መሸጥና ማከራየት እንደሚችል ሲሆን ስለሚሸጡት ቤቶች ብዛት የሚያወራው ነገር የለም። ዲቦራ ሁሉንም ቤቶች ቢሸጥ በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው ወደፊት አሰባስባቸዋለሁ ላላቸው የአእምሮ ዘገምተኞች የወር ወጪ በቋሚነት ገቢ ከየት ሊያመጣ ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተለያዩ ሸቀጦች እያመረቱ መሸጥ እንደሚችሉ በህግ የተፈቀደላቸው ቢሆንም መንግስት በነጻ በሰጣቸው መሬት ህንጻ ገንብተው የመሸጥ መብት ግን የላቸውም። እንደ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በህገ ወጥ መንገድ እንዲቆጠር የተደረገው ዲቦራ ፋውንዴሽን እዚህ ሌላ ችግር ገጠመው። ይህን ችግር ለማቃለል ሌላ አይን ያወጣ ህገ ወጥ ውሳኔ ዲቦራ ፋውንዴሽን ማስወሰን ነበረበት።

በ05 12 2015 እንደገና በ09 1 2016 በተጻፉ በደብዳቤዎች ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ዲቦራ ከመንግስት በነጻ ባገኘው መሬት ላይ ከአልሚዎች ጋር በመሆን የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለሶስተኛ አካል መሸጥ እንደማይችል ሲያውቀው፣ የክልሉን አስተዳደር ሌላ ውሳኔ እንዲውስንለት እንደጠየቀ ነው። የተጠየቀው ውሳኔ አስተዳደሩ ለበጎ አድራጎት ስራ የሰጠውን መሬት ከዲያቦራ ባላቤትነት ወደ ሌላ አካል ባለቤትነት እንዲቀየርለት ነው። ሌላው አካል ማን እንደሆነ አይታወቅም። ወደፊት የሚሰሩትን ቤቶች የሚገዙት ግለሰቦች በቀጥታ በግል ከተያዘ መሬት ላይ ቤት መግዛታቸውን የሚያሳይ ሰነድ እንዲዘጋጅላቸው፣ ከዛም ያለምንም የስም ማዛወር ክፍያ ባላቤት እንዲሆኑ የሚል ውሳኔ በደብዳቤው ላይ ተካቷል። ከሊዝ ክፍያ ነጻ የሆነ ለበጎ አድራጎት ስራ በሚል በህገወጥ መንገድ ለዲቦራ ፋውንዴሽን በከተማው እምብርት ላይ የተሰጠ 2148 ካሬ ሜትር ቦታ በዚህ አይነት መንገድ ወደ አባዱላና ሸሪኮቹ ኪስ እንዲገባ ተደርጓል። በዚህ በነጻ በተሰጠ መሬት ላይ የሚገነባው ህንጻ፣ ገቢው በቢሊዮኖች እንደሚሆን ይገመታል።

ይህን ህገ ወጥ ድርጊት መፈጸም የተቻለው በተረኛነት የክልሉን መስተዳደር በያዙት የኦሮሞ ብልጽግና ከፍተኛ ባለስልጣናት ቅንጅት ነው። ዶ/ር ቀንአ ያዴቴ ከመከላከያ ሚስቴርነት ለቆ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሃላፊ ሲሆን ቁልቁል የወረደ የመሰላችሁ ካላችሁ ተሳስታችኋል።

ሌላው ሁሉ ቀርቶ አባዱላ ገመዳ፣ በአእምሮ ዘገምተኝነት በምትሰቃየው ልጁ ስም ያቆመውን የበጎ አድራጎት ድርጅት ያለምንም የሞራል ልጓም እንዲህ ለዝርፊያ ሲጠቀምበት ስናይ ስለፋዎንዴሽኑ ብዙ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርገን ነው። እውን ፋዎንዲሽኑ የተቋቋመው ለበጎ አድራጎት ስራ ነው ወይንስ ለመሸቀያ? የሚደርሰን መረጃ የሚያሳየው አባዱላ ገመዳ የፋውንዴሽኑን ቢሮ ለደላላነት እንጂ ለተባለለት አላማ እየተጠቀመበት እንዳልሆነ ነው። ቀኑን የሚያሳለፈው በሚሊዮኖች ጉቦ እየተቀበለ የሃብታሞችን ጉዳይ ሲያስፈጽም እንደሚውል ነው።

የሚቀጥለውን ጥያቄ ብዙዎቻችን ለማንሳት እንገደዳለን። እናንተ ባታነሱት እኔ ለራሴ አነሳዋለሁ። ጥያቄው፣ በወያኔ ዘመን ተኮትኩተው ያደጉ አፋኞችና ዘራፊዎች በምን ተአምር ከዚህ ልክፍታቸው ነጻ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን አሰብን? ሌላስ እድል ሰጠናቸው የሚል ነው? ስለሌሎች መናገር ባልችልም አዲስ አበባ ላይ በተማርኩት አዲስ ቋንቋ “ሿሿ” ተሰርቼ ህዝብን ለሿሿ ሰሪዎች በማጋለጤ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ( አንዳርጋቸው ፅጌ)