የተፋጠጡ ፍልስጥኤማዊ ሴት እና እስራኤላዊ ወንድ

ከ 5 ሰአት በፊት

በመካከለኛው ምሥራቅ ፍልስጥኤም ለሁለት ተከፍላ የአረብ እና የአይሁዳውያን አገራት እንዲመሠረቱ ከተወሰነ በኋላ ፍጥጫ እና ጦርነት በተለያየ መጠን ሞቅ፣ ቀዝቀዝ እያለ ሲካሄድ ዘመናት ተቆጥረዋል።

በእስራኤል እና በፍልስጥኤማውያን ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጥቃት እና ጦርነት እየተደጋገመ የቀጠለ ቢሆንም፣ ባለፈው ቅዳሜ የተከሰተው ግን ከሌሎች ጊዜያት የተለየ በመሆኑ አሳሳቢ ሆኗል።

የፍልስጥኤሙ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የፈጸመው ድንገተኛ፣ የተቀናጀ እና መጠነ ሰፊ ጥቃት እስራኤላውያንን አስደንግጦ ቁጣን ቀስቅሷል።

ሐማስ ቅዳሜ ማለዳ በእስራኤል ይዞታዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ከማዝነብ ባሻገር ከሌላው ጊዜ በተለየ ታጣቂዎቹን ወደ እስራኤል አስርጎ በማስገባት ከባድ ጉዳትን አድርሷል።

እስራኤልም በአጸፋው በጋዛ ሰርጥ ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃት በማካሄድ በርካታ ፍልስጥኤማውያንን ከመግደሏ ባሻገር ከባድ ውድመትን አድርሳለች።

ይህ የሐማስ ጥቃት እና የእስራኤል የበቀል እርምጃ እስከ ምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ባይታወቅም፣ በአጭሩ የሚገታ አይመስልም።

ለመሆኑ ለዚህ የፍልስጥኤም-እስራኤል ፍጥጫ እና ጦርነት መነሻው ምንድን ነው? ሊያስማሟቸው ያልቻሉት ጉዳዮችስ የትኞቹ ናቸው።

1. የፍልስጥኤም-እስራኤል ግጭት እንዴት እና መቼ ጀመረ?

በዮርዳኖስ ወንዝ እና በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል ያለው እና በኦቶማን ቱርኮች ቁጥጥር ስር የነበረው የፍልስጥኤም አካባቢ በሙስሊሞች፣ በአይሁዶች እና በክርስቲያኖች ዘንድ እንደ ቅዱስ ቦታ የሚታይ ነው። አካባቢውም በአብዛኛው በአረቦች እና በሌሎች ሙስሊም ማኅበራሰቦች የተያዘ ሲሆን፣ አይሁዶችም ነበሩበት።

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ የኦቶማን ቱርኮች ግዛተ መንግሥት ሲፈራርስ፣ በወቅቱ የነበረው የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ብሪታኒያ የፍልስጥኤምን ግዛት እንድታስተዳድር ውክልና ሰጠ።

በተለያዩ ጊዜያት ብሪታኒያ በአካባቢው ላሉ አረቦች እና አይሁዳውያን የሚፈልጉትን እንደምታደርግ ቃል ብትገባላቸውም አንዱንም ባለመፈጸሟ ቅሬታና ውጥረት ተፈጥሯል።

አረቦች እና አይሁዳውያኑ በየበኩላቸው ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ በአረብ ብሔረተኞች እና በአይሁድ ጽዮናውያን መካከል ያለው ፍጥጫ ተባብሶ በሁለቱም ወገኖች በኩል ባሉ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች ተከሰቱ።

በአውሮፓውያኑ 1920ዎቹ እና 1940ዎቹ አውሮፓው ውስጥ ከሚደርስባቸው ጭቆና በመሸሽ እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአይሁዳውያን ላይ ከተፈጸመው የጅምላ እልቂት በኋላ መጠለያ አገር ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚገቡት አይሁዶች ቁጥር ጨመረ።

በዚያ ወቅትም በአይሁዳውያን እና በአረቦች መካከል ግጭቶች እየጨመሩ ሲመጡ በብሪታኒያ አስተዳደር ላይም ተቃውሞው ተጠናከረ።

በርካታ ፍልስጥኤማውያን የአይሁዶችን እርምጃ በመቃወማቸው በአካባቢው ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ የአጎራባች አረብ አገራትም ወታደሮችም ፍልስጥኤማውያንን በመደገፍ በጦርነቱ ተሳታፊ ሆኑ።

በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ቀያቸውን ጥለው ሸሹ ወይም ለቀው እንዲሄዱ ተገደዱ። ይህንንም ክስተት ፍልስጥኤማውያን “አል ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” ሲሉ ይጠሩታል።

በ1967 እአአ በተካሄደው የአረብ አስራኤል ጦርነት እስራኤል ከፍልስጥኤም ግዛቶች ባሻገር የጎረቤት አረብ አገራትን ይዞታዎች በወረራ ለመያዝ ችላለች።

ለስድስት ቀናት በተካሄደ ጦርነት እስራኤል በዮርዳኖስ እጅ የነበረውን ምሥራቃዊ የኢየሩሳሌም ክፍል፣ ግብፆች ያያዙትን የጋዛ ሰርጥን፣ የሶሪያን አብዛኞቹን የጎላን ተራሮችን እና የግብፅን ሲናይ ባሕረ ገብ መሬትን በእጇ አስገባች።

እስራኤል ግንቦት 14/1948 (እአአ) በይፋ ተመሠረተች
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል ግንቦት 14/1948 (እአአ) በይፋ ተመሠረተች

2. እስራኤል እንዴት በመካከለኛው ምሥራቅ ተመሠረተች?

በአይሁድ ትውፊት መሠረት አሁን እስራኤል የምትገኝበት ቦታ እግዚአብሔር ለአብርሃም እና ለዘሩ ቃል የገባው ምድር እንደሆነ ይታመናል።

አካባቢው በጥንታዊው ዘመን በተለያዩ ኃይሎች ተወሮ የቆየ ሲሆን፣ ስፍራውን ፍልስጥኤም ብለው የሰየሙት ሮማውያን እንደሆኑ ይነገራል። ከዚያም በኋላ በተካሄዱ ወረራዎች እና ማስገበሮች በአካባቢው በርካታ ለውጦች ተካሂደዋል።

እስራኤል እና ፍልስጥኤም ያሉበትን የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢን ይቆጣጠሩ የነበሩት ኦቶማን ቱርኮች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲሸነፉ አካባቢው በብሪታኒያ ቁጥጥር ስር ገባ።

መሬቱም ብዙኃን አረቦች እና አናሳ አይሁዳውያን የሚኖሩበት ነበር።

በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል አሁን ድረስ የዘለቀው ፍጥጫ የተባባሰው ብሪታኒያ በፍልስጥኤም ውስጥ የአይሁድ ሕዝቦች አገር መመሥረት የሚለውን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃዎችን መውሰድ ስትጀምር ነው።

አይሁዶች አካባቢው የአያቶቻቸው ርስት መሆኑን ሲያምኑ፣ የፍልስጥኤም አረቦች ደግሞ ግዛቱ የራሳቸው መሆኑን በመግለጽ ሃሳቡን ተቃወሙት።

ፍልስጥኤምን በሚመለከት የተዋቀረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ በአውሮፓውያኑ መስከረም 03/1947 ለጠቅላላ ጉባኤው ባቀረበው ሪፖርቱ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ የአይሁዳውያን አገር የመመሥረት ጥያቄ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ታሪካዊ” ምንጮችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሶ ነበር።

በተጨማሪም የብሪታኒያ መንግሥትም በፍልስጥኤም ውስጥ የአይሁዶች “አገር” መመሥረትን እንደሚደግፍ በ1917 (እአአ) ባወጣው የባልፎር ድንጋጌ ላይ አሳውቆ ነበር።

በአውሮፓ ውስጥ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ጊዜ እና ከዚያም በፊት በናዚዎች አማካይነት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ አይሁዶች ላይ በተፈጸመው የጅምላ እልቂቶች ምክንያት አገረ እስራኤል እንድትመሠረት እና እውቅና እንዲሰጣት ግፊት ሲደረግ ነበር።

በአረብ ብሔረተኞች እና በጽዮናዊነት እንቅስቃሴ አራማጆች መካከል ያለውን መካረር ለማርገብ ያልቻለችው ብሪታኒያ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሰደችው።

የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤም በኅዳር 29/1947 (እአአ) ፍልስጥኤም ለሁለት ተከፍላ ነጻ የአረብ እና የአይሁድ አገራት እንዲመሠረቱ የቀረበውን ሐሳብ ጸደቀ።

ይህንንም ተከትሎ ብሪታኒያ በፍልስጥኤም ላይ የነበራት ውክልና ከመጠናቀቁ አንድ ቀን በፊት ግንቦት 14/1948 (እአአ) አይሁዳውያን የእስራኤልን ነጻ አገርነትን አወጁ።

በቀጣዩ ቀንም እስራኤላውያን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ከአንድ ዓመት በኋላ ተቀባይነትን አገኙ።

የእስራኤል እና ፍልስጥኤማ ሰንደቅ አላማዎች

3. የፍልስጥኤም ግዛቶች ለምን ተነጣጠሉ?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የፍልስጥኤማውያኑ አረብ ግዛት የትኞቹን አካባቢዎች እንደሚያካትት በዝርዝር ቢያመለክትም፣ የመጀመሪያው የአረብ እስራኤል ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ ነበር ግዛታቸውው በግልጽ የለየው።

በዚህም በመካከላቸው የእስራኤል ግዛት የሚለያቸው ግራ እና ቀኝ በ45 ኪሎ ሜትሮች የተነጠሉ ሁለት የፍልስጥኤማውያን ግዛቶች ተፈጠሩ። አንደኛው ምሥራቃዊ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ዌስት ባንክ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የጋዛ ሰርጥ ሆነ።

ለረጅም ጊዜ በእስራኤል ወረራ ስር የቆየው እና አሁንም የአየር እና የባሕር እንቅስቃሴዎቹን እስራኤል የምትቆጣጠረው የጋዛን ሰርጥን ደቡባዊ ድንበር በእጇ አስቀርታ ለፍልስጥኤማውያን የመለሰችው በአውሮፓውያኑ 2005 ነበር።

በአሁኑ ወቅት የጋዛ ሰርጥን በፍልስጥኤም አንጃዎች እና በእስራኤል መካከል የተፈረሙ ስምምነቶችን በማይቀበለው በእስላማዊው ቡድን ሐማስ አስተዳደር ስር ነው የሚገኘው።

በሌላ በኩል ደግሞ ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው እና ዋነኛው ፓርቲ ፋታህ ሲሆን ይህም የፍልስጥኤም መንግሥት ተብሎ ነው የሚጠራው።

4. ፍልስጥኤም እንደ አገር ዕውቅና አላት?

በመንግሥታቱ ድርጅት አማካይነት ፍልስጥኤም ለሁለት ተከፍላ የአረብ እና የአይሁድ አገራት እንዲመሠረቱ ከወሰነ በኋላ እስራኤል የራሷን መንግሥት መሥርታ በዓለም ላይ ካሉ አገራት አንዷ ለመሆን ችላለች። ፍልስጥኤም ግን እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ለዚህ አልታደለችም።

እስራኤል በተመሠረተች በዓመት ውስጥ እንደ አንድ አገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ስትሆን፣ ፍልስጥኤም ግን “አባል ያልሆነች ታዛቢ አገር” በመሆን የድርጅቱ ሙሉ የአባልነት ቦታን አላገኘችም።

እንደ አገር የመንግሥታቱ ድርጅት ሙሉ አባል ለመሆን ጥያቄ ብታቀርብም ከፀጥታው ምክር ቤት አባላት በቂ ድጋፍ ባለማግኘቷ ጉዳይዋ ተንጠልጥሎ ቀርቷል።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አባል ከሆኑት 193 አገራት መካከል 138ቱ ወይም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፍልስጥኤምን አገርነት በይፋ ዕውቅና ሰጥተዋል።

ኢየሩሳሌም
የምስሉ መግለጫ,ፍልስጥኤማውያን እና እስራኤላውያንን ከማያስማሙ ጉዳዮች መካከል የኢየሩሳሌም ጉዳይ ዋነኛው ነው

5. የማያስማሟቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ለዘመናት በእስራኤል እና በፍልስጥኤም መካከል ስምምነት እንዳይደረስ ምክንያት የሆኑ በርካታ ምክንያቶች አሁንም በመካከላቸው እንቅፋት ሆነው አፋጠዋቸው ይገኛሉ። ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡

ፍልስጥኤማውያን ስደተኞች፡ በተለያዩ አገራት ውስጥ ተበትነው የሚገኙት ስደተኞች ጉዳይ አንዱ ነው። ዋነኛው የፍልስጥኤሞች ፖለቲካ ፓርቲ ፒኤልኦ 10.6 ሚሊዮን ዜጎቹ በስደት እንዳሉ ይጠቅሳል። ከእስራኤል ጋር ለመስማማት አሁን እስራኤል ወደሚባለው ግዛት መመለስ አለባቸውም ይላል። አስራኤል ደግሞ ይህ የአይሁድ ማንነቷን አደጋ ላይ ይጥላል በማለት አትቀበለውም።

የእስራኤላውያን ሰፈራዎች፡ እስራኤል ከ1967 (እአአ) ጦርነት በኋላ በወረራ በያዘቻቸው የፍልስጥኤማውያን ግዛቶች በሚባሉት በምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና በዌስት ባንክ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያንን አስፍራለች። በእስራኤል መንግሥት የተገነቡት እነዚህ የሰፈራ አካባቢዎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ተብለው ተነቅፈዋል። ፍልስጥኤማውያን አይሁድ ሰፋሪዎች ከግዛታቸው እንዲወጡ ቢጠይቁም እስራኤል ሳትቀበለው ቆይታለች።

የድንበር ጉዳይ፡ ፍልስጥኤማውያን የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱ አገራት እንዲመሠረቱ ሲወስን ያስቀመጣቸው ግዛቶች እንዲከበሩ፣ ለዚህም እስራኤል ከ1967ቱ የአረብ እስራኤል ጦርነት በፊት ወደነበረ ይዞታዋ እንድትመለስ ይፈልጋሉ። እስራኤል ግን ይህንን አትቀበለውም።

የኢየሩሳሌም ባለቤትነት፡ እስራኤል ከተማዋ ሉዓላዊ ግዛቷ እንደሆነች እና በ1967ቱ ጦርነት ምሥራቃዊውን ኢየሩሳሌም ከተቆጣጠረች በኋላ ኢየሩሳሌም ዋና ከተማዋ መሆኗን በይፋ ብትገልጽም ዓለም አቀፍ ዕውቅና አላገኘችም። ፍልስጥኤማውያን ደግሞ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም መዲናቸው እንድትሆን ይፈልጋሉ።