
ከ 4 ሰአት በፊት
በእስራኤል እና ጋዛ ያለው ሁኔታ ከመካከለኛው ምስራቅ የሚነሳውን የነዳጅ አቅርቦት ሊያስተጓጉል ይችላል በሚል ስጋት ዛሬ ሰኞ የነዳጅ ዋጋ በ4 በመቶ አሻቅቧል።
የአሜሪካን የነዳጅ ዋጋ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ዌስት ቴክሳስ ኢንተርሚዲየት የተሰኘው ተቋም የነዳጅ ዋጋን ወደ 86 ዶላር ከፍ አድርጓል።
የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋም በእስያ ገበያ ጨምሯል።
እስራኤልና ፍልስጤም ነዳጅ ላኪ ባይሆኑም መካከለኛው ምስራቅ የዓለምን አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን ነዳጅ ያቀርባል።
ባለፈው ቅዳሜ የሐማስ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ ሁለቱ ኃይሎች የገቡበት ሁኔታ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው።
ምዕራባውያን ጥቃቱን አውግዘዋል። የሐማስ ቃልአቀባይ ቡድናቸው ከኢራን ቀጥተኛ ድጋፍ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
ሆኖም ትላንት በኒው ዮርክ በተካሄደው የመንግሥታቱ ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ላይ ኢራን ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ማለቷ ተዘግቧል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኃይል አቅርቦት ተንታኙ ሳውል ካቮኒክ በጋዛ የተፈጠረው ሁኔታ በአቅራቢያ በሚገኙት ዋነኛ የነዳጅ አምራች በሆኑት ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ይላሉ።
“ግጭቱ ሐማስ እየደገፈች ነው የምትባለውን ኢራንን የሚያካትት ከሆነ የዓለም 3 በመቶ የነዳጅ አቅርቦት ስጋት ላይ ይወድቃል” ሲሉም አክለዋል።
- የእስራኤል-ፍልስጥኤምን ፍጥጫ እና ጦርነት ለመረዳት አምስት ቁልፍ ጥያቄዎችከ 5 ሰአት በፊት
- የእስራኤል የስለላ ተቋማት መጠነ ሰፊውን የሐማስ ጥቃት እንዴት ሳይደርሱበት ቀሩ?8 ጥቅምት 2023
- ቀጥታ፡ በእስራኤል እና በጋዛ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ ሆነ8 ጥቅምት 2023
ተንታኙ በተጨማሪም የመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ዋነኛ መተላለፊያ የሆርሙዝ የባህር ወሸመጥ በግጭቱ ምክንያት ከተስገጓጎለ የዓለም አንድ አምስተኛ ገደማ የሚሆነው ነዳጅ “ሊታገት” ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የሆርሙዝ የባህር ወሸመጥ ምጣኔ ሀብታቸው በነዳጅ ላይ ለተመሰረቱ የገልፍ ሀገራት ቁልፍ መስመር ነው።
ነገሮች ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመሩ በማይታወቅበት በቀጣዮቹ ቀናት የአሜሪካ የቦንድና ዶላር ኢንቨስትመንት ሊጨምር ይችላል ተብሏል። ይህ ኢንቨስትመንት ቀውሶች በሚያጋጥሙ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።
ሩስያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ120 ዶላር በላይ ተሽጧል።
በቅርቡ የድፍድፍ ነደጅ ዋጋ እየወረደ በበርሜል 70 ዶላር አከባቢ መሸጥ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የነዳጅ ምርት አቅራቢዎች አቅርቦት ለመቀነስ ከሞከሩ በኋላ ዋጋው ዳግም ማሻቀብ ጀምሯል።
ከፍተኛ ነዳጅ አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ዕለታዊ ነዳጅ ምርቷን በሚሊዮን እንደምትቀንስ አስታውቃ ነበር።
ሌሎች የነዳጅ አምራች ሀገራት ህብርት የሆነው ‘ኦፔክ ፕላስ’ አባላትም ዋጋን ለመጨመር በማለም ምርት ለመቀነስ እየሞከሩ ነው።
የ‘ኦፔክ ፕላስ ’ አባል ሀገራት የዓለም ድፍድፍ ነደጃ አቅርቦቷን 40 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ውሳኔያቸው የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእዕኖ ያደርጋል።