
ከ 5 ሰአት በፊት
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን ምግብ እርዳታ ለስደተኞች በማቅረብ ሲጀምር ለኢትዮጵያውያን ተረጂዎች አቅርቦቱን ለመጀመር በሙከራ ላይ መሆኑን አስታወቀ።
ድርጅቱ የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ለሚገባቸው ተጠቃሚዎች ሳይደርስ ለሌላ አላማ እየዋለ ነው በሚል ነበር ባለፈው ዓመት እርዳታው እንዲቋረጥ ያደረገው።
የመንግሥታቱ ድርጅት አካል የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምግብ እርዳታውን መልሶ የጀመረው “በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የስደተኛ ካምፖች የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ዋነኛ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ” እንደሆነ ገልጿል።
የድርጅቱ ረዳት ሥራ አስፈጻሚ ቫሌሪ ጓርኔሪ እንደተናገሩት “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች የምግብ እርዳታ የሕይወታቸው መሠረት ነው፤ በአሁኑ ወቅት የእርዳታ አቅርቦቱን ለመጀመር የሚያስችሉንን ወሳኝ እርምጃዎች ተግባራዊ በማድረጋችን እፎይታ ሰጥቶናል” ብለዋል።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተቋረጠው የምግብ እርዳታ መልሶ መጀመር 900 ሺህ ለሚጠጉ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ አቅርቦት መልሶ እንዲጀመር ማድረጉን ድርጅቱ ገልጿል።
ኢትዮጵያ በአብዛኛው ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኤርትራ የመጡ 850 ሺህ ስደተኞች የሚገኙባት ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ ከሱዳን የመጡ ወደ 35 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ድርጅቱ ገልጿል።
- የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ ያቋረጠውን እርዳታ ለስደተኞች ብቻ እንደሚጀምር አስታወቀ6 ጥቅምት 2023
- የተባበሩት መንግሥታት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ አቋረጠ10 ሰኔ 2023
- የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ማቋረጥ ‘ፖለቲካዊ’ እርምጃ ነው ሲል ተቃወመ10 ሰኔ 2023
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምግብ ስርጭት በሰባት ክልሎች ውስጥ የሚጀመር ሲሆን ተጠቃሚዎች ጥራጥሬ፣ የአትክልት ዘይት እና ጨው እንዲያገኙ እንደሚደረግ እና ሌሎች ደግሞ ከሚገባቸው ድጋፍ ከፊሉን በገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
የእርዳታ አቅርቦቱ ለተጠቃሚዎች እንዲውል ለማስቻል በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ያሉ 24 የምግብ መጋዘኖች በዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የተረጂዎች መረጃ በዘመናዊ ሁኔታ ቁጥጥር ይደረገብታል ተብሏል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም አሁን የእርዳታ አቅርቦቱን የጀመረው ለስደተኞች ብቻ ነው። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የምግብ እርዳታ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን የሚያቀርበውን ድጋፍ ለመጀመር የሚያስችለው ሥርዓት በሙከራ እና በትግበራ ሂደት ላይ መሆኑን አመልክቷል።
ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ አቋርጦ የነበረው የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ተራድ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ለስደተኞች የሚሰጠውን ድጋፍ መልሶ ለመጀመር መወሰኑን ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር።
ይህ የምግብ እርዳታ አቅርቦትን መልሶ ለመጀመር በዩኤስኤአይዲ የተደረሰው ውሳኔ ሁሉንም የእርዳታ ፈላጊዎች የሚመለከት ሳይሆን፣ በአገሪቱ ላሉት ስደተኞች የሚደረገውን እርዳታ ብቻ መልሶ በመጀመር ላይ ያተኮረ ነው።
ዩኤስኤአይዲ እርዳታውን ለመጀመር የወሰነው የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ የስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መዋቅር ላይ ለውጦችን በማድረጋቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች የምግብ እርዳታን የማጓጓዝ፣ የማከማቸት እና የማሰራጨት ኃላፊነትን ለሌሎች አጋሮች በማስተላለፉ” መሆኑን ገልጿል።
ሁለቱ ተቋማት ከአራት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ሲያቀርቡ የነበረውን የምግብ እርዳታ እንዲቋረጥ ያደረጉት መጠነ ሰፊ የተቀናጀ የእርዳታ አቅርቦት ላልተገባ አላማ የማዋል ድርጊት በመፈጸሙ መሆኑን በግለጽ ነው።
በተከታታይ ድርቅ፣ በጦርነት እና በግጭቶች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት መረጃ ያመለክታል።
