October 10, 2023 – Konjit Sitotaw
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 13 ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ሊያዘዋውሩ የሞከሩ 2 ፖሊሶች ተያዙ።
በኬንያ ቱርካና 8 ኢትዮጵያውያን፣ 4 ኤርትራውያንን እና 1 ሱዳናዊ ስደተኞችን አሳፍረው ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የኬንያ ፖሊስ ስደተኞቹንም በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለፀ ሲሆን ስደተኞቹ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በቱርካና እንደተሻገሩ እና መዳረሻቸውን ደብብ አፍሪካ ለማድረግ አስበው እንደነበር ተናግረዋል።
የኬንያ ፖሊስ እና የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ለመጓዝ ሲሞክሩ በተደጋጋሚ በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ ሲገልፁ ኬንያን ተሻግረው ወደ ሌላ ሃገር ለመሻገር ሲሞክሩ የሚያዙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም አሳውቀዋል።
በኬንያ በየዓመቱ በአስር የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሌላ ሀገር ለመሻገር በሚሞክሩበት ጊዜ እንደሚያዙና ከሀገሪቱን እንደሚባረሩ ፖሊስ ሲገልፅ ፥ በኬንያ የተሻለ የስራ እድል ለማግኘት አስበው ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ስደተኞች መኖራቸውም ነው የተገለፀው።
በሀገሪቱ የሚገኙ የወንጀል ክፍል ኃላፊዎች ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ ሲገልፁ ፥ በቅርቡ አንድ ኢትዮጵያዊ በኬንያ 12 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማዘዋወር ወንጀል የ31 ዓመት እስራት እንደተፈረደበት አስታውሰዋል።
Source: The Star , Pulse Kenya
