የሰሜን ሸዋ ዞን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ “ከሰሞኑ ያወጣሁትን ዘገባ ከበላይ አካል በደረሰብኝ ጫና አንስቻለሁ” አለ
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ “ከወሎ እና ከሰሜን ሸዋ ዞን ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ድብደባ እና ዝርፊያ ተፈጽሞባቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል” በሚል ያወጣነውን ዘገባ፤ ከበላይ አካል በደረሰብን ጫና እንድናነሳ ተገደናል ሲል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ባለሙያ፤ “ሰሞኑን ከአማራ ክልል ደሴና አካባቢው እንዲሁም ከደብረ ብርሃን መናኸሪያ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተጓዦች፤ ከኦሮሚያ ክልል እስከ አዲስ አበባ ባሉት አገር አቋራጭ መንገዶች ዘረፋና ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
በተጓዦች ላይ የደረሰውን ዘረፋና ድብደባ በተመለከተ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን መንገደኞች በደብረብርሃን መናኸሪያ እና አካባቢው ተዘዋውረን አነጋግረን ዘገባ ሰርተን ነበር ሲል መምሪያው አሳውቋል፡፡
“ዘገባውን በዞኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የማሕበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የለጠፍን ቢሆንም፤ የዞን እና የክልሉ የበላይ ኃላፊዎች ባደረሱብን ጫና ዘገባውን እንድናነሳ አስገድዶናል፡፡” ብለዋል፡፡
በማሕበራዊ ትስስር ገጾቻቸው አጋርተውት የነበረው ዘገባ ምንም አይነት ስህተት የሌለበት እንደነበርም የጠቆሙ ሲሆን፤ ድብደባና ዘረፋ የተፈጸመባቸው ተጓዦች የአማራ ክልል መታወቂያ የያዙ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ የተፈመው ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ በምትገኝ ሸኖ ከተማ ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
“ከድብደባው የተረፉት ተጓዞች ለምግብና መጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ፤ በደብረብርሃን መናኸሪያ ውስጥ ሌሎች ተጓዞችን ርዳታ ሲጠይቁም አስተውለናል፡፡” ብለዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የደብረ ብርሃን መናኸሪያ የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ቡድን መሪ ስዩም ተፈራ በበኩላቸው፤ “ሰሞኑን ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተጓዦች ድብደባ እና ዝርፊያ፣ ደርሶባቸዋል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከ3 ሺሕ በላይ ተጓዦች መመለሳቸውን እና ከእነዚህም ውስጥ አስራ አንድ ተሳፋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ከተከለከሉት ሰዎች መካከል የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በብዛት እንደሚገኙበት ገልጸው፤ ድርጊቱ ትናንት ሰኞ መስከረም 29/2016 ቀጥሎ መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡
