October 10, 2023 

በኦሮሚያ ክልል ከ750 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በምስራቅ የኦሮሚያ ክፍል ከ750 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አክሞን ኢኒሺዬቲቭ ዴቬሎፕመንት የተሰኘ የበጎ አድራጎት ተቋም ባወጣቸው ጥናት አመላክቷል፡፡

በተለይም ከአራቱ የወለጋ ዞኖች ማለትም ከምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መድረሱ ተገልጿል፡፡

እነዚህ ተፈናቃዮች በ11 ዞኖች እና 96 ወረዳች ሥር ባሉ 141 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል 753 ሺሕ 674 የሚሆኑት አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸው ተወስቷል፡፡

እነዚሁ ተፈናቃዮች ከአንድ አንድ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በኃይል እንዲወጡ እየተደረጉ መሆናቸውን ጥናቱ ገልጿል፡፡

በተለይም በቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና ምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉ ሰዎች ከአራት ወራት በፊት ግንቦት ወር 2015 ላይ ከመጠለያ ካምፑ እንዲወጡ መደረጋቸው ያወሳው ጥናቱ፤ እነዚሁ ሰዎች ለረሀብ፣ ለበሽታ እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን መጥቀሱን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች፡፡

ተፈናቃዮቹ የመጡበት አካባቢ በመንግሥት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ለተከታታይ ዓመታት ውጊያ ሲደረግበት የነበረበት እና አሁንም እየተደረገ ያለበት ቦታ በመሆኑ ወደ ቄያቸው መመለስ የማይታሰብ መሆኑም ተነግሯል፡፡

ለተከታታይ አምስት ዓመታት ሲደረግ በነበረው በአራቱም የወለጋ ዞኖች በቀጠለው ግጭት በየዕለቱ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻንቡ ካምፓስ፣ በሆሮ ጉዱሩ ዞን መናኸሪያ፣ በሻንቡ ከተማ ስታዲየም እና በምስራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ ሥፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችም በተመሳሳይ አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ መኖራቸው ተነግሯል፡፡