October 10, 2023 

ኦነግ ሸኔ በደራ ወረዳ 16 የገጠር ቀበሌዎችን መቆጣጠሩ ተገለጸ

 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ 16 የገጠር ቀበሌዎች በኦነግ ሸኔ ቁጥጥር መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የኦነግ ሸኔ አባላት በተለይም ከባለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ወደ ወረዳዋ በስፋት በመግባት 16 የሚጠጉ የገጠር ቀበሌዎችን እንደተቆጣጠሩ ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በተቆጣጠራቸዉ የገጠር ቀበሌዎችም በርካታ ንጹኃን በአሰቃቂ ኹኔታ እንደተገደሉ፤ ንብረታቸዉ እየተዘረፈባቸዉና ቤታቸዉ በእሳት እየወደመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደራ ወረዳን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘዉ መንገድ በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ሥር በመዋሉ፤ ዜጎች በነጻነት እንዳይቀሳቀሱ እና መሰረታዊ ሸቀጦችም እንዳይገቡ ከተደረገ ብዙ ጊዜያትን አስቆጥሯል ተብሏል፡፡

ይህ መስመር መዘጋቱን ተከትሎ የወረዳዋ ነዋሪዎች በአማራ ክልል መርሃቤቴ ከተማ በኩል ወደ አዲስ አበባ ሲገቡና ሲወጡ የነበረ ቢሆንም፤ በአማራ ክልል ባለዉ ወቅታዊ ኹኔታ ምክንያት መስመሩ ዝግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ከጸጥታዉ ችግር በተጨማሪ ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀዉስ ዉስጥ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይም በመንገዱ መዘጋት የጤና አገልግሎት ችግር መፈጠሩን እና ነብሰ ጡር እናቶች ጭምር ሕይወታቸዉን እያጡ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በወረዳዋ የገጠር ቀበሌዎች የሚኖረዉ ሕዝብ የታጣቂ ቡድኑን ጥቃት ለመሸሽ ወደ ወረዳዋ ዋና ከተማ ጉንዶ መስቀል እየተፈናቀለ በመሆኑ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንዳልተቻለም ነዋሪዎች አውስተዋል፡፡

የወረዳው አስተዳዳር በበኩሉ የታጣቂ ቡድኑን ጥቃት ለመመከት በቂ የጸጥታ ኃይል እንደሌለው የተናገረ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በኦነግ ሸኔ ተደጋጋሚ ጥቃትን ሲያስተናግድ የቆየዉ የወረዳው ሕዝብ አሁንም ንጹኃን ዜጎችን እየገደለ፣ እያፈነ፣ ንብረት እያወደመና እያቃጠለ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሺበሺ አያሌዉ እንደተናገሩት፤ “ታጣቂ ቡድኑ ንጹሃን ላይ ጥቃት መክፈቱን እና በተለይም በ8 ቀበሌዎች በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አረጋግጠናል፡፡” ብለዋል፡፡

ይህ ቡድን በወረዳዋ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከኹለት ዓመት በላይ እንደተቆጠረ የተናገሩት ሺበሺ፤ “ታጣቂ ቡድኑን ለማስወጣት በወረዳዋ ያለዉ የጸጥታ ሃይል በቂ አይደለም” ማለታቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል፡፡

በሽብር ቡድኑ መንገድ መዝጋትና በአማራ ክልል ባለዉ ወቅታዊ ኹኔታ በተዘጉት ኹለቱ መንገዶች ምክንያት፤ በወረዳዋ የተፈጠረዉን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ቀዉስ ለመፍታት ከሚመለከተዉ አካል ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡