የዓለምን ክብረ ወሰንን የሰበረ ዱባ

ከ 2 ሰአት በፊት

ማይክል ጆርዳን የሚል ስያሜ የተሰጠው ግዙፍ ዱባ ከ1200 ኪሎ ግራም በላይ በመመዘን የዓለምን ክብረ ወሰን ሲሰብር፣ ዱባውን ያመረተው ግለሰብ ደግሞ 30 ሺህ ዶላር ተሸለመ።

በአሜሪካ ሜኒሶታ ግዛት ውስጥ በግብርና ምርቶች ዘርፍ መምህር የሆነው ታራቪስ ጂንጅር ያመረተው ዱባ ከዚህ ቀደም ትልቁ ተብሎ የተመዘገበውን እና 21 ኪሎ ግራም የሚመዝንውን ዱባ በከፍተኛ ልዩነት በመብለጥ ነው ክብረ ወሰኑን የሰበረው።

ይህ ግዙፍ ዱባ 1247 ኪሎ ግራም በመመዘን እስካሁን በምድር ላይ ከተመረቱት ዶባዎች በላይ ሆኖ ነው የዓለምን ክብረ ወሰን መያዝ የቻለው።

በካሊፎርኒያ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የዱባ ክብደት ሻምፒዮና ሽልማቱን የወሰደው ጂንጀር አሸናፊነቱ የፈጠረበት ስሜት “በጣም ከባድ ነው” ብሏል።

መምህሩ ዱባውን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ተጨማሪ እንክብካቤ ያደርግ እንደነበር የገለጸ ሲሆን፣ በቀንም እስከ 12 ጊዜ ውሃ ያጠጣው እንደነበር ተናግሯል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ጂንጀር ማይክል ጆርዳን ሲል የጠራውን ዱባ ባለፈው ሚያዚያ ወር የተከለው ሲሆን፣ ፍሬውን ለመንከባከብ 15 ሺህ ዶላር አውጥቶበታል።

ከዚያም በተሽከርካሪው ጭኖ ለውድድሩ ወደ ካሊፎርኒያ አቅንቷል።

የ43 ዓመቱ ግለሰብ ከታዳጊነቱ ጀምሮ ዱባዎችን የሚያበቅል ሲሆን፣ የዱባ ክብደት ሻምፒዮናን ሦስት ጊዜ አሸንፏል።

ይህ ውድድር እንደ ውሮፓውያኑ በ1974 እንደ ጨዋታ የተጀመረ ነው። አጀማመሩም በኦሃዩ እና ካሊፎርኒያ ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች መካከል የዓለም የዱባ መገኛ ነን የሚል “ፉክክርን” መሠረት ያደረገ ነው።

አዘጋጆቹ አሁን ውድድሩን ወደ ዓለም አቀፍ የዱባ ክብደት ውድድር አሳድገውታል።

አሸናፊው ዱባውን ለምን በማይክል ጆርዳን ስም እንደሰየመው ሲገልጽ፣ ጆርዳን የምንጊዜም ምርጥ ቅርጫት ኳስ ተጨዋች ነው፣ ካለ በኋላ ዱባውም የምንጊዜም ትልቁ ነው ብሏል።

ጨምሮም ጆርዳን 23 ቁጠር መለያ እንደሚለብስና አሁን በፈረንጆች አቆጣጠር ያለውን ዓመት 2023 ለማመሳል እንዳደረገውም ተናግሯል።

“በሰዎች ፊት ላይ ፈገግታን ለመፍጠር ይህን ሰርቻለው” ሲሉም ለአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።