አፋር ውስጥ በግጭት በወደመ አካባቢ የምትታይ ታዳጊ
የምስሉ መግለጫ,አፋር ውስጥ በግጭት በወደመ አካባቢ የምትታይ ታዳጊ

11 ጥቅምት 2023, 12:03 EAT

ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ወታደሮች እና በአካባቢ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ውጊያ ምክንያት በአገሪቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት አማካሪ አስጠነቀቁ።

የድርጅቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ የሆኑት አሊስ ዋይሪሙ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ላይ እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ “ከፍተኛ የዘር ማጥፋት እና ተያያዥ ወንጀሎች የመከሰት አደጋ አለ” ብለዋል።

በትግራይ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ያበቃ ቢሆንም፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከተባባሰ ወራት ተቆጥረዋል።

በተለይ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረገው ግጭት ተባብሶ በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። አሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳሉ እየተነገረ ነው።

ልዩ አማካሪዋ ጉዳዩን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ነገሮችን በተመለከተ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች “በጣሙን የሚረብሹ እና እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ማቅረብ የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብለዋል።

እንደ ምሳሌም የአንድ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ስለመገደላቸው፣ ሰዎች በቤተሰባቸው አባል ላይ ዘግናኝ ወንጀል ሲፈጸም እንዲመለከቱ ስለመደረጋቸው፣ አንድ ሙሉ ማኅበረሰብ ስለመፈናቀሉ ወይም ከመኖሪያው ስለመባረሩ ሪፖርቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ቡድኖች በማንነታቸው ምክንያት ተለይተው ለጥቃት ኢላማ እንደሚዳረጉ እና ለዚህም በሚያመች ሁኔታ ስም እንደሚለጠፍባቸው አማካሪዋ ምሳሌዎችን ጠቅሰው፣ በዚህም “የዘር ማጥፋት አደጋ መኖሩን እና ስጋቱ እየጨመረ መምጣቱን” አመልክተዋል።

ጨምረውም በትግራይ እና በአማራ ክሎች ውስጥ መጠነ ሰፊ የመድፈር እና ሌሎች አይነት ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቀደም ባለው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት መገለጹ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተጨባጭ እየተባባሱ የሚሄዱ የደኅንነት ስጋቶች እና የመብት ጥሰቶች መኖራቸው እንዳሰሰበው ማመልከቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በአገሪቱ “በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ከፍተኛ ስጋቶች አሉ” ያለ ሲሆን፣ እነዚህም የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን ጠቅሷል።

መርማሪ ኮሚሽኑ ጨምሮም ለእነዚህ ወንጀሎች ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁሉም ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ከእነዚህም ውስጥ ቀጣይነት ያላቸው ከባድ የመብት ጥሰቶች፣ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች፣ አለመረጋጋት እና ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ ስጋቶች ናቸው ብሎ ነበር።

ልዩ አማካሪዋ በበኩላቸው በኮሚሽኑ የተጠቀሱት እየቀጠሉ ያሉት አስጊ ሁኔታዎች “በእጅጉ እንዳሳሰባቸው” በሪፖርታቸው ላይ አመልክተዋል።

ጨምረውም ግጭትን ለማስቆም ከአንድ ዓመት በፊት የተደረሰው ስምምነት በአብዛኛው ውጤት እንዳላስገኘ ገልጸው፤ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በቀጠሉበት ሁኔታ እየጨመሩ የሚሄዱ የጭፍጨፋ ክሶች፣ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጸሙ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄዱ ውጊያዎች፣ እንዲሁም “የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ሚሊሻዎች አባላት ትግራይ ውስጥ ከባድ የመብት ጥሰት መፈጸም ስለመቀጠላቸው የሚያመለክቱ ሪፖርቶች የሚረብሹ ናቸው” ብለዋል አሊስ ዋይሪሙ።

አክለውም በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተጣለበት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አንስቶ “በርካታ ተዓማኒነት ያላቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰት ሪፖርቶች” መውጣታቸውን በማንሳት ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ልዩ አማካሪዋ አሳስበዋል።

አሊስ ዋይሪሙ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እየታዩ ያሉ የመብት ጥሰቶች እንዲቆሙ እና ለተፈጸሙትም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ አጋዥ መሆኑን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር እርምጃ መውሰድ አለባት ብለዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለው አሳሳቢን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ የሚጠበቅባቸውን በማድረግ ሊከሰት ይችላል ያሉትን አደገኛ ሁኔታ ለማስቀረት አስተዋጽኦ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።