
October 11, 2023

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ሊያካሂድ የነበረው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ በጥቂት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ተሳትፎ ብቻ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲተላለፍ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳሰበ።
ሚኒስቴሩ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው በንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ለመሳተፍ የሚያበቃውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ የንግድ ምክር ቤቱ አባል ምክር ቤቶች ቁጥር አነስተኛና ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የማያስችል በመሆኑ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መሳተፍ ከሚገባቸው አባል ምክር ቤቶች መካከል ለመሳተፍ የሚያበቃቸውን ቅድመ ሁኔታ ሊያሟሉ የሚችሉት ጥቂቶቹ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ምክር ቤቱ በተወሰኑ አባላት ብቻ ጠቅላላ ጉባዔውንም ሆነ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለምክር ቤቱ ቤቱ ማሳወቁን ሪፖርተር ከምክር ቤቱ ያደረሰው መረጃ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ለተከታታይ ዓመታት ሳያካሂድ የቆየውን ጠቅላላ ጉባዔ፣ ዘንድሮ መካሄድ እንደሚኖርበት በቦርዱ ተወስኖ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፣ በጠቅላላ ጉባዔው ለመሳተፍ ያሳወቁ አምስት አባል ምክር ቤቶች ብቻ ቢሆኑም፣ ምክር ቤቱ በእነዚሁ አባላት ብቻ ምርጫውን ለማካሄድ ወስኖ ነበር፡፡ ከአምስቱ አባል ምክር ቤቶች ውስጥም ተገቢውን ፎርማሊቲ አሟልተው የቀረቡት የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ብቻ መሆናቸው በመረጋገጡ ጉባዔውን ለመጥራት ያልተቻለ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መሳተፍ ከሚኖርባቸው ከ18 በላይ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ውስጥ በጉባዔው ለመሳተፍ የሚፈለገውን መሥፈርት ያሟሉ አባላት 25 በመቶ እንኳን ባለመሆናቸው ጠቅላላ ጉባዔው ተሠርዟል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር ጉባዔው ቀሪ እንደማይሆን አስታውቆ ነበር፡፡፡
ለአባል ምክር ቤቶችም በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ምርጫ አድርገው የአባላቶቻቸውን ቁጥርና ሌሎች ማሟላት የሚገባቸውን መረጃ አደራጅተው ሪፖርት እንዲያደርጉ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሪፖርት ያደረጉት አምስት ብቻ መሆናቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ የአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤቱ ሥራ አመራር ቦርድ ፎርማሊቲውን ባሟሉት አምስት አባላት ብቻ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን ለማካሄድ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህ ውሳኔው ግን በሚኒስቴሩ ተቀባይነት ሊያገኝ ባለመቻሉ የታቀደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዲራዘም አስገድዷል፡፡ ይህም ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ሳያካሂድ የዘገየበት ጊዜ የበለጠ እንዲራዘም ከማድረጉም በላይ ቀጣዩን ጉባዔ ለመጥራት አሁንም የሚኒስቴሩ ውሳኔ የሚጠበቅ ስለመሆኑም የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ እንደማይችል ከውሳኔ ላይ የደረሰው፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መገኘት አንችልም ያሉ አባል ምክር ቤቶች የሰጡትን ምክንያት ጭምር ከመረመረ በኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አባል ንግድ ምክር ቤቶች በጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ሊካሄድ በታቀደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ላለመገኘት የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበው እንደነበር ምክር ቤቱ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ መካከል በጠቅላላ ጉባዔው ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው ሁለት የክልል ምክር ቤቶቸ መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በክልሉ በተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ እንደማይችል በማሳወቁ ነው፡፡
አንዳንዶቹም በአገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመገኘት የሚያስችላቸውን ጠቅላላ ጉባዔዎች ለማካሄድ የተሰጣቸው ጊዜ አጭር በመሆኑ፣ በአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገሩ ማሳወቃቸው ተጠቅሷል።
የበጀት እጥረት አለብን ብለው ያመለከቱም አሉ ተብሏል፡፡ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ደግም ባጠናሁት ጥናት በሥሩ ያሉ አባል ምክር ቤቶች ምርጫ ለማካሄድ ስድስት ወራት እፈልጋለሁ ብሎ አሳውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ ንግድ ምክር ቤቶች ዝግ ባልሆኑበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ ሊደገፍ አልቻለም፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ፣ ምክር ቤቱ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ቁርጥ አቋም ቢይዝም፣ ከጠቅላላ አባል ምክር ቤቶቹ 25 በመቶ እንኳን በማይሞሉ አባላቱ ጉባዔውን ለማካሄድ መነሳቱ አግባብ አልነበረም ይላሉ፡፡ አብዛኛውን አባል ምክር ቤቶች ተሳታፊ ያላደረገ ጉባዔተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ መነሳቱም ከሕግ አኳያም ቢሆን አግባብ እንዳልነበረ ይጠቅሳሉ፡፡
በመሆኑም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሰጠው ውሳኔ ክልከላው አግባብ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዳይካሄድ የተባለው ጠቅላላ ጉባዔ፣ በቀጣይ መቼ ሊደረግ ይገባል የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባም እኚሁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ የቆየው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከዚህም በኋላ እንዳይረዝም ሚኒስቴሩ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ሊካሄድ ለታቀደው ጠቅላላ ገባዔን ምርጫ ለማካሄድ አባል ምክር ቤቶቹ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው የአባሎቻቸውን ቁጥር እንዲያሳውቁ የተሰጣቸው ጊዜ ከሁለት ወራት ያልበለጠ በመሆኑ፣ አብዛኛዎቹ አባል ምክር ቤቶቹ ዝግጁ ባለመሆናቸው፣ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለመወከል የሚያስችላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንዳያሟሉ አድርጓቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመወከልና እንደ ከዚህ ቅደሙ ባላቸው አባላት ልክ ድምፅ እንዲኖራቸው ማድረግ ከተፈለገ፣ ከወዲሁ እንዲዘጋጁ ማሳሰብ እንደሚገባም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በሌላ በኩል ግን የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ረቂቅ በአሁኑ ወቅት በፍትሕ ሚኒስቴር ታይቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከ በመሆኑ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ ስለሚጠበቅ ቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲሱ አዋጅ መሠረት ሊከናወን ይችላል የሚል ግምት አላቸው፡፡ ሆኖም ቀጣዩን ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት አሁንም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ውሳኔ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ በተለያዩ ምክንቶች እየዘገየ መሄድ ግን በተለይ በጠቅላላ ጉባዔ መወሰን ያለባቸው ትልልቅ ጉዳዮች በእንጥልጥል እንዲቆዩ እያደረገ ስለመሆኑም ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ገልጸዋል፡፡
ለአብነት ያህል የሚጠቀሰውም የደቡብ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አለመቻሉ ነው፡፡ ከደቡብ ክልል የወጡ አዳዲስ ክልሎች መፈጠር ጋር ተያይዞ በተለይ የሲዳማ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ራሱን ችሎ ቢቋቋምም፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ለመሆን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አዳዲስ የንግድ ምክር ቤቱን አባላት ለመቀበል ውሳኔው የጠቅላላ ጉባዔ በመሆኑ ነው፡፡ ሌሎች የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔዎች የሚጠብቁ ጉዳዮች በተመሳሳይ ባለፉት አራት ዓመታት ሳይካሄዱ መቅረታቸው የጠቅላላ ጉባዔ አለመካሄድ እየፈጠረ ያለውን ተፅዕኖ አመላክተዋል፡፡.
