
ከ 4 ሰአት በፊት
ከኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን፣ ሂትሮ አየር ማረፊያ ሲጓዝ የነበረ የኬንያ አውሮፕላን “በደህንነት ስጋት ምክንያት” ማረፊያውን እንዲቀይር ተገደደ።
አውሮፕላኑ በዩኬ አየር ኃይል ተዋጊዎች አማካኝነት ማረፊያውን ቀይሮ በምስራቅ ብሪታንያ በምትገኘው በኢሴክስ ከተማ፣ ስታንስቴድ አየር ማረፊያ እንዲያርፍ ተደርጓል።
የለንደን ስታንስቴድ ቃል አቀባይ የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላን የሆነው ቦይንግ 787 አውሮፕላን የኢሴክስ ፖሊሶች በተገኙበት በሰላም ማረፉን ገልጸዋል።
“አውሮፕላኑ እጀባ ተደርጎለት ራቅ ወዳለ ስፍራ ተወስዶ መደበኛ ስራውን እያከናወነ ” እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢሴክስ ፖሊስ አሁን ላይ ነገሮች መረጋጋታቸውን አስታውቋል።
ፖሊስ ምርመራ ተደርጎ ምንም የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ አውሮፕላኑ ቀድሞ ወደታሰበበት አውሮፕላን ማረፊያ መመለሱን ገልጿል።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አየር ኃይሉ ትላንት ከሰዓት ወደ ዩኬ እየቃረበበ የነበረውን አውሮፕላን በነበረው ስጋት ክትትል እንደተደረገበት ገልጸዋል።
አውሮፕላኑ እስከ ስታንስቴድ አየርመንገድ እጀባ ተደርጎለት የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩ መረጋገጡን ተናግረዋል።
ጨምረውም አሁን ክስተቱ በሲቨል አስተዳደሮች ክትትል ስር እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የኢሴክስ ፖሊስ በበኩሉ ከናይሮቢ ወደ ለንደን ሂትሮ አየር ማረፊያ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን አቅጣጫውን ወደ ስታንስቴድ አየር ማረፊያ እንዲቀይር መደረጉን ገልጿል። አየር ማረፊያው ለአገልግሎት ክፍት መደረጉንም አንስቷል።
- እስራኤል 1.1 ሚሊዮን ፍልስጥኤማውያን ከጋዛ በ24 ሰዓታት ይውጡ አለች- ተመድ8 ጥቅምት 2023
- እስራኤል የምትመካበት የሚሳኤል እና የሮኬቶች ማምከኛ ‘አይረን ዶም’ ምንድን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- የተመድ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ላይ ያወጡትን መግለጫ እንዲያስተባብሉ መንግሥት ጠየቀ12 ጥቅምት 2023

የኬንያ አየር መንገድ በበኩሉ ትላንት በረራ ላይ የነበረው አውሮፕላን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት አለው የሚል ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ገልጿል።
“የኬንያ አየር መንገድ አመራር በሚደረገው የስጋት ፍተሻ ላይ ከኬንያ እና ከዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ጋር በጋራ እየሰራ ነው። በበረራ ላይ ያሉት ሰራተኞችም ገለጻ ተደርጎላቸዋል። ቀደም ብሎም ለበረራ ሰራተኞችና ለተሳፋሪዎች አስፈላጊው የደህንነት ቅድመ ጥንቃቄ ተደርጓል” ብሏል።
የኬንያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢላን ኪላቩካ “በረራ ላይ በነበሩ አንዳንድ ሰዎች ላይ ጥርጣሬ ነበር። ነገር ግን ከቦምብ ወይም ከመሰል ነገር ጋር አይገናኝም” ብለዋል።
“የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ የወስድንበት ምክንያት ስጋቱ በመጨመሩ ነው። ስለዚህ ምንም የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩን እርግጠኛ ለመሆን ነው ያደረግነው” ሲሉም አክለዋል።
የኢሴክስ ፖሊስ ስታንስቴድ አየር ማረፊያ በዩናየትድ ኪንግደም እንዲህ አይነት የበረራ ደህንነት ስጋት በሚያጋጥምበት ወቅት የደህንነት ስራዎችን ለመስራት የተለየ ማረፊያ እንደሆነ አረጋግጧል።
የመከላከያ ሚኒስቴርም ይሁን የኢሴክስ ፖሊስ በጥርጣሬው ምክንያት እንዲቆይ የተደረገ ተሳፋሪ ስለመኖሩ ያሉት ነገር የለም።
