በኢትዮጵያ 31 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ
(አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ እየተባባሰ በቀጠለው ዘርፈ ብዙ ችግር ምክያት፤ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር 31 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም ዓቀፍ የሕጻናት ነፍስ አድን ፈንድ (ዩኒሴፍ) አስታውቋል፡፡
ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ኹኔታ አስመልክቶ ትናንት ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ 31 ነጥብ 4 ሚሊየን ያህል ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጸ ሲሆን፤ ከነዚህ ዉስጥ 16 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሆኑት ሕጻናት መሆናቸውን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ችግሮች የሰው እጅ ጠባቂ የሆኑ ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፤ በአገሪቱ 4 ነጥብ 38 ሚሊየን የአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች እንዲሁም 942 ሺሕ 792 የሚሆኑ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖራቸውንም አመላክቷል፡፡
ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ አስቸኳይ ሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት 674 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ያለ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 255 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚያደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሁም፤ 345 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በድርቅ ለተጎዱ በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፍ የሚውል መሆኑን ገልጿል፡፡
ከዚህም የገንዘብ መጠን ውስጥ እስካሁን ያገኘው 187 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን የገለጸው ዩኒሴፍ፤ ይህም የሕይወት አድን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 28 በመቶውን ብቻ ይወክላል ብሏል፡፡
ዩኒሴፍ በባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች 25 ነጥብ 3 ሚሊዮን መድረሳቸውን አስታውቆ እንደነበር አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ ይድርጅቱ ሪፖርት በአገሪቱ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር በ6 ነጥብ 1 ጨምሮ 31 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱን የሚያመላክት ነው፡፡
ድርጅቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሕይወት አድን ሥራውን ለማስፋት ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ገንዘብ እንዲያቀርቡም ተማጽኖ አቅርቧል፡፡
