ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት ዕሴቶችንና ጥቅምን ለመበየን ያለሙ ሰነዶች ተዘጋጁ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት ዕሴቶችንና ጥቅምን ለመበየን ያለሙ ሰነዶች ተዘጋጁ

ሰላማዊት መንገሻ

ቀን: October 15, 2023

ሰላም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነትንና ዕሴቶችን እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅሞችን ለመወሰን ያለሙ መነሻ ረቂቅ ሰነዶችን ማዘጋጀቱ ታወቀ።

ብሔራዊ ማንነት ስለአንድ አገር ባለቤትነት ወይም የይገባኛል ወይም ደግሞ የትስስር ስሜት ደረጃን የሚያሳይ ሲሆን፣ የብሔራዊ ዕሴት ዋነኛ መገለጫው ደግሞ አገርን የሚገልጹና የሚያሳውቁ የጋራ እምነቶችና መርሆዎችን መፍጠር እንደሆነ ያስረዳል።

ብሔራዊ ማንነትና ብሔራዊ እሴት ሁለት የተለያዩ ፅንሰ ሐሳቦች ቢሆኑም፣ የጋራ የሚያደርጓቸው አረዳድ፣ ባህሪ፣ ምንጭና ብያኔዎች መኖራቸውን የሚያስረዳው ይህ ሰነድ፣ ሁለቱም ፅንሰ ሐሳቦች ዜጎች ስለአንድ አገር ያላቸውን አመለካከትና እነርሱ በዚያ አገር ስላላቸው ሥፍራ የሚኖራቸውን መረዳት የሚወስኑ ሐሳቦች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡

የጋራ አገራዊ ማንነት ዕጦት በማኅበረሰብ ውስጥ ለሚከሰቱ ተቃርኖዎች አለፍ ሲልም በተለያዩ ማንነት ተከታዮች መካከል ለሚፈጠሩ መራርና ደም አፋሳሽ ግጭቶች አንዱ መነሻ እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ እነዚህን ተቃርኖዎች በዘላቂነት ማስታረቅ ዘርፈ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ሲሆን ተቃርኖዎቹ እንዳይሰፉና በየዘርፋቸው በሚፈጥሩት የተናጠል ትርክት አገራዊ አንድነት እንዳይዳከም የጋራ ማንነት መገንባት መቻል ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆን እንዳለበትም ያመለክታል።

በርከት ያሉ አገሮች ብሔራዊ ማንነታቸውን ከመርሆዎችና ከፖለቲካ ዕሳቤዎች ተነስተው መቅረጻቸውን፣ ሌሎች አገሮች ደግሞ ብሔራዊ እሴቶቻቸውን ከባህል፣ ከትውፊትና መሰል አገራዊ መገለጫዎች እንደቀዱ ሰነዱ ይገልጻል። በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ እሴትና ማንነታቸውን ከሁለቱም ምንጮች የቀዱ አገሮች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ 

በኢትዮጵያ አገራዊ ማንነትን በተጨባጭ እንዴት መረዳት እንደሚገባ፣ ከምን ምንጮች ሊቀዳ እንደሚችል፣ ምን ምን ጉዳዮች አገራዊ ማንነት ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ በተወሰነ መልኩ የሚጠቁም ምክረ ሐሳብን ሰነዱ የያዘ ሲሆን፣ ብሔራዊ ማንነትን መገንባት ምን ሒደቶችን አልፎና ዳብሮ ቢተገበር ይበልጥ ስኬታማ ይሆናል የሚለውን የሚያመላክት አጭር ምክረ ሐሳብም ሰነዱ አካቷል።

‹‹ኢትዮጵያ የብዝኃ ሥልጣኔ፣ ብዝኃ መሠረት (ፋውንዴሽን)፣ ብዝኃ ባህልና ብዝኃ እምነት ማንነቶች ባለቤት የሆነች አገርና ልዩ፣ ልዩ ማኅበረሰቦቿም ለሺዎች ዓመታት ወደኋላ ሄደው የሚተርኩት ታሪክና ሥልጣኔ ያላቸው በመሆናቸው፣ መገንባት ያለበት ብሔራዊ ማንነት የአንዱን አካትቶ የአንዱን ትቶ ፈጽሞ ሊሳካ ሰለማይቻል የብሔራዊ ማንነት ግንባታ ውጥን በቅድሚያ የኢትዮጵያን ብዝኃነት እንደ አገሪቷ ዋና ማንነት መመልከት ይገባዋል›› ይላል ሰነዱ፡፡  

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ማንነትን ለመለየት ከላይ የተቀመጠውን መሠረታዊ ታሳቢ ነጥብ ከግንዛቤ በማስገባት፣ ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ማንነታቸው ለይተው ለመበየን በጋራ ቢመክሩባቸው ያላቸውን አላባዊያን ለመነሻነት ጠቁሟል።

በግንባር ቀደምነት የቀረበው ብዝኃነት ሲሆን፣ የሃይማኖቶች፣ የታሪክ፣ የሥልጣኔዎች፣ የቋንቋዎች፣ የባህሎች፣ የማኅበራዊ ሀብቶች፣ የመልክዓ ምድሮች፣ የአየር ጠባያት፣ የአስተዳደር ሥርዓቶች፣ የልዩ፣ ልዩ ስልተ ምርት፣ ወዘተ ባለቤት አገር መሆኗ አንዱ የጋራ ማንነቷ ሰበዝ መሆኑን ይጠቁማል። ሌላው የኢትዮጵያ ‹‹ምድረ ቀደምትነት›› ሲሆን፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ለመላ አገሪቱና ለዓለም ጭምር መነሻ የሆኑ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አበርክቶዎች ያሏት አገር መሆናኗ። የራሷ የዘመን መቁጠሪያ፣ የጊዜ አቆጣጠር፣ ፊደልና አሃዝ ባለቤት የሆነች፣ ከቀደምት የዓለም ሥልጣኔዎች መገኛ መሆኗ ሌላኛው የኢትዮጵያ የጋራ ማንነት ሰበዝ ሊሆን አንደሚችል ጠቋሟል። 

ነፃነት (ቅኝ አለመገዛት፣ ነፃነትን የሚሻ ሕዝብና አገር፣ ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት)፣ እንግዳ ተቀባይነት (ከአገሪቷ ፈላሲያንን የማስተናገድ ረዥም ታሪክ፣ ማኅበረሰቦቿ ካሏቸው እሴቶችና ሌሎች የውጭ ተመልካቾችም ሕዝቦቿን ከሚገልጹባቸው መልኮች አንጻር የሚጠቀስ ወሳኝ ማንነት መሆኑ)፣ የሃይማኖት የታሪክ ሀብታም፣ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ማንነቶች ያሏት አገር፣ የዓባይ ወንዝ መነሻ የሚሉት ሰነዱ ብሔራዊ ማንነትን ለመበየን በጥቆማ መልክ ያቀረባቸው ናቸው።

ብሔራዊ ዕሴትን ለመፍጠር ካቀረባቸው ጥቆማዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ነው።

‹‹ኢትዮጵያ የብዝኃነት ምድር ብቻ ሳትሆን ብዝኃነታቸውን በኅብር (harmony) ተከባብረውና ተሳስረው የሚኖሩባት አገር የምንመኘው (desirable value) ብቻ ሳይሆን መሆን ያለበትና ሊተገበር የሚችል (desired value) እሴት ሲሆን ከአገረ መንግሥቱ ግንባታ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ዕድሜ ጠገብ አጨቃጫቂ የታሪክ አረዳዶች ብሎም የፖለቲካ መቆራቆሶች እልባት እንዲያገኙ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት እሴት ነው›› ሲል ሰነዱ ለመጀመሪያ ጥቆማው ማብራሪያ ሰጥቶበታል።

ብሔራዊ ዕሴትን ለመገንባት ከተጠቆሙት አላባዊያን መካከል እንደ ኅብር (Harmony)፣ ፍትሐዊነት፣ አርበኝነት፣ ወንድማማችነት/እህትማማችነት፣ ታታሪነት የሚሉት ይገኙበታል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት ዴስክ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን፣ ሚኒስቴሩ ከተቋቋመበት አዋጅ በመነሳት እነዚህን ሰነዶች እንዳዘጋጃቸው ገልጸዋል። የሰላም ሚኒስቴር የተቋቋመበት አዋጅ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር ኃላፊነትን እንደሰጠው ጠቁመዋል። 

‹‹ከግንዛቤ ዕጥረት የተነሳ ከሐገራዊ ጥቅም በተጻራሪ የምንቆምበት ሁኔታ አለ። ይህ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው። ስለዚህ የጋራ አቋም ልንይዝባቸው የሚገቡ የአገር ጥቅሞች ላይ መረዳትን ለመፍጠር ነው። ምክንያቱም ምሰሶ የሆኑ አገራዊ ጥቅሞች ከተነኩ አገር ይፈርሳል›› ብለዋል።

በመነሻ ሰነዱ ላይ ከምሁራን ጋር ምክክር ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ገዛኸኝ፣ በቀጣይም በነዚህ ሰነዶች ላይ ከማኅበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎበት እንደሚዳብር ተናግረዋል።

ሰነዶቹ የውይይት መነሻ መሆናቸውን፣ በወይይት ከተመከረባቸው በኋላ ደግሞ ወደ ፖሊሲ ሰነድነት ወይም ወደ ሕግ ማዕቀፍነት ተሸጋግረው በተለያዩ አስፈጻሚ አካላት በዘላቂነት እንዲተገበሩ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል።

የተዘጋጁት ሰነዶች ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባርና ኃላፊነት ጋር የሚደጋገፍ እንጂ የሚቃረን እንዳልሆነም ጠቅሰዋል። የምክክሩ ኮሚሽኑ ኃላፊነት በጊዜ የተገደበና በምክክሩ የሚፈልቁ ሐሳቦችን የማስፈጸም ኃላፊነት እንዳልትሰጠው የገለጹት አቶ ገዛኸኝ፣ ከዚህ ሰነድና ከምክክር ኮሚሽኑ የሚፈልቁትን ሐሳቦች በዘላቂነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።