
ዜና በአገር ደኅንነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት እንዳይገባ በአዋጅ ሊከለከል ነው
ቀን: October 15, 2023
- ተቆጣጣሪው አካል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍተሻ ማድረግ ይፈቀድለታል
በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት ወደ አገር እንዳይገባ፣ እንዳይወጣና ጥቅም ላይ እንዳይውል በአዋጅ ሊከለከል ነው።
በዚህም መሠረት ለኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ሥጋት የሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ክልከላ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሐሙስ፣ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ የሆኑ አዎንታዊ ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም፣ በአንፃሩ የራሱ የሆኑ የተለያዩ አሉታዊ ጎኖችም እንዳሉት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ሥጋቶች የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ከመጣስ ባለፈ፣ ከምንጊዜውም በላይ በአገሮች ደኅንነትና ጥቅም ላይ ሥጋት እየደቀኑ መሆኑን ሪፖርተር የተመለከተው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ሰነድ ያስረዳል።
ከቴክኖሎጂ የሚመነጩ ሥጋቶች ከዓመት ወደ ዓመት እጅጉን እየጨመሩ የሄዱ ሲሆን፣ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በ2020 ባወጣው የሥጋት ሪፖርትም (Global Risks Report) በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የዓለም ሥጋቶች ምንጮች ተብለው ከተለዩት አሥር ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች መሆናቸውን ማብራሪያ ሰነዱ ይገልጻል።
በአሁኑ ጊዜ በርካታ ዘመኑ ያፈራቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች መደበኛ በሆኑ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና መደበኛ ባልሆኑ የአገሪቱ አዋሳኝ ድንበሮች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡና እየወጡ መሆኑን፣ ነገር ግን እነዚህ የቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ሥጋት ደረጃ ሕግን መሠረት አድርጎ በአግባቡ ተለይቶ ያልታወቀ ከመሆኑም በላይ የደኅንነት ሥጋት በሚፈጥሩት ላይ ግልጽ ክልከላ ወይም ገደብ ሳይጣልባቸው መቆየቱን ያስረዳል። ለእነዚህ የቴክኖሎጂ ምርቶች ተገቢው የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥርዓት ካለመዘርጋቱ ጋር ተዳምሮ፣ የግለሰቦችን ነፃነት ከመገደብ ጀምሮ ለአገር ደኅንነትና ጥቅም የሥጋት ምንጭ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ ክፍተቱን የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ መፍታት አስፈላጊ እንደሆነ ያመለክታል።
ሪቂቅ አዋጁ በአራት ክፍሎችና በ22 አንቀፆች ተከፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የረቂቅ አዋጁ ክፍል አንድ ለተለያዩ ቃላቶች የተሰጡ ትርጓሜዎችን ይዟል። በዚሁ መሠረት ለረቂቅ አዋጁ መሠረታዊ ለሆነው ‹‹የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት›› ለሚለው ስያሜ፣ ‹‹የኤሌክትሮኒክ ዳታዎችንና ሲግናሎችን ለማነፍነፍ፣ ለማስተጓጎል፣ ለመጥለፍ፣ ለመደምሰስ፣ ለማሳሳት፣ ለማወክ፣ ለመስረቅና ተዓማኝነት ለማሳጣት የሚያስችልና በኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሥጋት ሊፈጥር የሚችል የቴክኖሎጂ ቁስ፣ ንድፍ፣ ስልተ-ቀመር፣ ዘዴ፣ አገልግሎት ወይም መተግበሪያን ያጠቃልላል፤›› የሚል ትርጓሜ ተሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ሥጋት›› እና ‹‹ክልከላ የተደረገበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት›› ለሚሉት ሐረጎች ረቂቅ አዋጁ የሕግ ትርጓሜያቸውን አስቀምጧል።
በረቂቅ አዋጁ ትርጓሜ መሠረትም የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ሥጋት ማለት፣ ‹‹ኢንፎርሜሽን በሚሰበሰብበት፣ በሚተነተንበት፣ በሚከማችበት፣ በሚሠራጭበት ወይም ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት ተዓማኒነቱን፣ ሚስጥራዊነቱንና ተደራሽነቱን ሊያሳጡ የሚችሉ ሥጋቶች፤›› አንደሆነ ተመላክቷል።
‹‹ክልከላ የተደረገበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት›› ለሚለው ደግሞ፣ ‹‹በአገራዊ የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር በዚህ አዋጅ መሠረት ወደ አገር እንዳይገባ፣ ከአገር እንዳይወጣ ወይም ጥቅም ላይ እንዳይውል ሙሉ ክልከላ የተጣለበት የቴክኖሎጂ ምርት ነው›› የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ፣ ‹‹ገደብ የተደረገበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት›› ለሚለው ሐረግ፣ ‹‹በኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር፣ በዚህ አዋጅ መሠረት አግባብነት ባለው የደኅንነት ማረጋገጫ ፈቃድ ብቻ ወደ አገር እንዲገባ፣ ከአገር እንዲወጣ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውል ገደብ የተደረገበት የቴክኖሎጂ ምርት ነው፤›› የሚል ትርጓም ተቀምጧል።
በረቂቅ አዋጁ ክልከላና ገደብ ለሚጣልባቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች ጥቅል ትርጓሜ የተሰጠበት ምክንያት በየጊዜው ከሚኖረው የቴክኖሎጂ ዕድገትና ተለዋዋጭነት አንፃር ሁሉንም ሥጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂ ምርቶችን ዘርዝሮ ማቅረብ አዳጋች በመሆኑ ነው።
በመሆኑም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ክልከላና ገደብ የሚጣልባቸው የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለይቶ ዝርዝራቸውን በመመሪያ እንደሚያወጣ በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል።
በሚወጣው መመሪያ ክልከላ ወይም ገደብ የሚጣለባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ዝርዝር አስተዳደሩ በየዓመቱ ከቴክኖሎጂ ዕድገትና ተለዋዋጭነት አንፃር ማሻሻያ እንዲያደርግ እንዲሁም፣ በኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሥጋት ወይም አደጋ የሚፈጥሩ አዲስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ወደ አገር በሚገቡበት ወይም ከአገር በሚወጡበት ወቅት ተጨማሪ ክልከላ ወይም ገደብ የመጣል ሥልጣን እንደሚኖረው ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል።
በተጨማሪም አስተዳደሩ ክልከላ ወይም ገደብ የሚደረግባቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ዝርዝር በዌብ ሳይትና በተለያዩ አማራጮች ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ክልከላና ገደብ የተጣለባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ በመግቢያና መውጫ በሮች ቁጥጥር የሚያደርጉ እንዲሁም ክልከላና ገደብ የተጣለባቸው ምርቶች በሕገወጥ መንገድ በማንኛውም ቦታ ስለመኖራቸው ወይም ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ ጥርጣሬ በሚኖርበት ወቅት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተቆጣጣሪ አካላትን እንደሚሰይም ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።
ተቆጣጣሪ አካሉ ክልከላና ገደብ የተጣለባቸው ምርቶች ስለመኖራቸው ወይም ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ ጥርጣሬ ያለው እንደሆነ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ቦታው በመግባት ፍተሻና ምርመራ የማድረግ ሥልጣን እንደሚኖረው በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል።
ከላይ የተጠቀሰው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስፈላጊነት ቢኖርም፣ የኢንፎርሜሽን ደኅንነትን ላይ አደጋ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠርና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስኪወጣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቱ ወይም አስፈላጊ መረጃዎች ሊጠፋ፣ ሊበላሽ፣ ወይም ሊሸሸግ እንደሚችል ተቆጣጣሪ አካሉ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖረው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማንኛውም ቦታ የመግባትና የመፈተሽ ሥልጣን ይኖረዋል። ነገር ግን ተቆጣጣሪ አካሉ በ48 ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያው ለሚገኝ ፍርድ ቤት የማሳወቅ ግዴታ የሚጣልበት ይሆናል።
ተቆጣጣሪ አካሉ ክልከላና ገደብ የተጣለባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ሕገወጥ በሆነ መልኩ ስለመያዙ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር ማንኛውንም ማጓጓዣ አግባብነት ካላቸው የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የማስቆም፣ የመፈተሽና ምርቱን የመያዝ ሥልጣን እንደሚኖረውም በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል።
የተከለከሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን በመጠቀም ማንኛውንም ቁጥጥር የሚደረግበትን ተግባር ማከናወን እንዲሁም፣ የፀና ደኅንነት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖር ገደብ የተደረገበትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርትን በመጠቀም ማንኛውንም ቁጥጥር የሚደግበትን ተግባር ማከናወን የተከለከለ መሆኑንም ሪቂቅ አዋጁ ያመለክታል።
ማንኛውም ሰው እነዚህን ክልከላዎች ተላልፎ የተከለከሉ ተግባራትን የፈጸመ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራትና ከሃምሳ ሺሕ እስከ መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል። ድርጊቱ በቸልተኛነት የተፈፀመ ከሆነ እና በአገርና በዜጎች ደኅንነት ላይ ጉዳት ካላደረሰ፣ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል አስራትና እስከ ሃምሳ ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣም ያመለክታል።
ነገር ግን ድርጊቱ በተደራጀ መልኩ የተፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፀኑ እስራትና ከመቶ ሺሕ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚያስቀጣ ከረቂቅ አዋጁ ለመራዳት ተችሏል።
ረቂቅ አዋጁ ሲጸድቅ በመላው የኢትዮጵያ ግዛት ተፈጻሚ እንደሚሆን ነገር ግን የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ፌዴራል ፖሊስ እንደማይመለከታቸው ተመላክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን በመጀመሪያ ንባብ ከተመለከተ በኋላ በዝርዝር እንዲታይ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
