
<ትግራይ እያለቀሰች ነው> – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ <ዛሬ በትግራይ ክልል የማይለቀስበት ቤት የለም> ሲሉ ተናግረዋል።
ፓትርያርኩ ይህን ያሉት በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ሕይወታቸውን ላጡት እየተከናወነ ላለው የሀዘን ሥነ ሥርዓትን አስመልክቶ ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ ላይ ነው።
<< በትግራይ ክልል እየተዘከሩ ላሉት ወገኖች በእጅጉ ማዘናችንን እንጋልጣለን >> ያሉት አቡነ ማትያስ <ይህ እንዳይመጣ ብዙ ተማፅኖ ስናቀርብ ነበር> ሲሉ አስታውሰዋል።
ይሁንና <ሽበት እና ክህነት የማይከበርበት ዘመን ላይ ደርሰን ለዚህ ሀዘን በቅተናል> ሲሉ ወቀስዋል።
የፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መልዕክት ሲቀጥል ታሪክ መስራት የሚችሉ የሀገር ተስፋዎች በእሸት በመቅረታቸው < በሀዘን በተሰበረ ልብ > በመሆን ለነፍሳቸው እረፍትን ተመኝተዋል።
<በኀዘን የተጎዳችሁ አባቶችና እናቶችም ይህ ቢሆን ኖሮ እያላችሁ ራሳችሁን እንዳትጎዱ፤ የእናንተ መጎሳቆል የሞቱትን ቀና አያደርግም> ያሉት አቡነ ማትያስ << ልባችሁን እንድታበረቱ እናሳስባለን ምክንያቱም መቃብር መጨረሻችን ያልሆነ የትንሣኤ ሕዝብ ነን> ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሰላም ዋጋ መሆኑን ካለፉት የፈተና ጊዜያት በመማር <ከጦርነቱ የተረፉት በሰላም የመኖር መብታቸው እንዲከበር፣ አረጋዊያን በክብር እንዲጦሩ፣ ህፃናት በትምህርት እንዲያድጉ> ጥሪ አስተላልፈዋል። ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም <የሰማዕታት የሃዘንና የክብር ቀን ሥነ-ስርዓት> በትግራይ ክልል ሲከናወን ውሏል።
