Ethiopia Insider
· ቪዲዮ:- በትግራይ ክልል ከትላንትና ጀምሮ የታወጀውን የሀዘን ቀን እና የመርዶ ስነ ስርዓት ተከትሎ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ፖለቲከኞች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ህይወታቸውን ላጡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጸሎት እና የጧፍ ማብራት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት አከናውነዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የሰባት ሀገራዊ እና ክልላዊ ፓርቲዎች አመራሮች እና አባላት ተገኝተው ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በትግራይ ክልል የደረሰው ሀዘን የጋራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ የአማራ እና የአፋር ዜጎችን ጭምር ለማሰብ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሀዘን ቀናት ሊታወጅ ይገባ እንደነበር ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የነበረው “የእርስ በእርስ መገዳደል” በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም ክልሎች መቀጠሉ የሚያሳዝን እና መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ እንደሆነም ፖለቲከኞቹ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የኢህአፓ ጽህፈት ቤት በተካሄደው በዛሬው ስነ ስርዓት ላይ መልዕክቶቻቸውን ካስተላለፉት ውስጥ፤ የሀዘን ቀን ባታወጀበት ትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) እና የትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ (ትሰእፓ) አመራሮች ይገኙበታል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ (አኢዴፓ) አመራሮችም እንዲሁ መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል። ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገለሉ የቀድሞ አመራሮች እና አባላት፤ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው የሀዘን መልዕክቶቻቸውን አስደምጠዋል።
(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)