October 16, 2023 

ኤርትራ የባህር በር ጉዳይ ላይ ለድርድር እንደማትቀመጥ አስታወቀች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተነሳዉ የባህር በር ጉዳይ ላይ፤ ኤርትራ ለድርድር እንደማትቀመጥ የኤርትራ መንግሥት የመረጃ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት የመረጃ ሚኒስትር ዛሬ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ “በቅርብ ጊዜ ስለ ውሃ እና ስለ ባህር በሮች እንዲሁም ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች የተነገረው እና የተባለው ቁጥር የለውም” ያለ ሲሆን፤ “በዚም ያልተገረመ ታዛቢ የለም” ብሏል፡፡

የኤርትራ መንግሥትም እንደኹልጊዜው በእንደዚህ ዓይነቱ ጉዳዮች ላይ ለውይይት እንደማይታደም ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፤ ይህ ነገር ይመለከተናል የሚሉ ኹሉም አካላት ጉዳዩን እንዳይነኩት በመግለጫው ማሳሰቡን የኤርትራ መንግስት መረጃ ያመላክታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አርብ ጥቅምት 2/2016 ምሽት፤ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈውና ‹‹ከጠብታ ውኃ እስከ ባሕር ውኃ›› የሚል ርዕስ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ባደረጉት ገለጻ፤ ቀይ ባህርን አስመልክተው ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በመግለጫቸውም፤ “በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በዘር (በብሄር) እና በኦኮኖሚ ምክንያቶች የቀይ ባህር ጉዳይ ይመለከተናል።” ያሉ ሲሆን፤ “ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንጂ ቅብጠት አይደለም። አባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ልማትና ጥፋት የሚወስኑ የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ናቸው።” ብለዋል፡፡