October 16, 2023 – Konjit Sitotaw 

የሱዳን ጦር ሰራዊት እና የፈጥኖ ደራሹ ሀይል ተወካዮች በድብቅ በአዲስ አበባ ተገናኝተዋል ተባለ

የሱዳኑ የስለላ ድርጅት ዳይሬክተር ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ ጊዜው የፈጥኖ ደራሹ ሀይል አማካሪ አዲስ አበባን ከጎበኙበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ከምንጮቼ ተረድቻለው ሲል አሽራቅ አልአውሳት ዘግቧል።

የሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አህመድ ኢብራሂም አሊ ሙፍዲል እና የፈጥኖ ደራሹ ሀይል የህግ አማካሪ መሀመድ አልሞክታር በአዲስ አበባ በተገናኙበት ወቅት በሱዳን ስላለው ጦርነት መወያየታቸውም ተገልጿል።

እንደ ዘገባው ከሆነ ኹለቱ ባለስልጣናት በአካባቢው ስላለው ኹኔታ እንዲሁም እየተካሄደ ባለው ጦርነት የመላ አገሪቱን ጸጥታና ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ ተጽዕኖዎች አጽንኦት ሰጥተው መነጋገራቸውን ተጠቁሟል።

የሱዳን ጦር መሪዎች ከፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮ ጦርነቱን ለማቆም ማሰባቸውም ተመላክቷል።

በተመሳሳይ ዜና የሱዳን ጦር ሠራዊት የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በአገሪቱ ጦርነት የተፈጸሙ አለም ዓቀፍ ወንጀሎችን የሚያጣራ መርማሪ አካል ለማቋቋም መወሰኑን ውድቅ ማድረጉ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።

ተቃዋሚው የነጻነትና ለውጥ ኃይሎችና ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በበኩላቸው የአጣሪ ቡድን ማቋቋም ውሳኔውን የደገፉ ሲሆን፤ የነጻነትና ለውጥ ንቅናቄ፣ በጦርነቱ የተፈጸሙ ወንጀሎች ለዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት እንዲመሩ ጭምር መጠየቁ ተመላክቷል።

ወታደራዊው መንግሥት “የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት ብሪታኒያና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ምክር ቤቱን የራሳቸውን ዓላማ ማራመጃ አድርገውታል፡፡” በማለት የከሰሰ ሲሆን፤ የጦር ሠራዊቱ፣ “አለም ዓቀፍ የጥሰት ምርመራ ማነጣጠር ያለበት በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ላይ ብቻ ነው፡፡” ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።