
ከ 4 ሰአት በፊት
ናይጄሪያ ውስጥ የሞተ ሰውን የራስ ቅል ከመቃብር ስፍራ ቆፈረው በማውጣት ወንጀል የተከሰሱ አምስት ሰዎች የ12 ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
ሃብታም ለሚያደርጋቸው የአምልኮ ሥርዓት ማስፈጸሚያ አስፈላጊ ነው በሚል ወደ ጠንቋይ ለመውሰድ ሲሉ ነው የራስ ቅሉን ከተቀበረት ስፍራ በማውጣት ሊወስዱት አስበው ነበር ተብሏል።
ግለሰቦቹ (ሁሉም ወንዶች ናቸው) የራስ ቅሉን በከረጢት ይዘው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል።
ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ከሆነ ግለሰቦቹ ከሦስት ዓመት በፊት በሰሜን ማዕከላዊ ናይጀር ግዛት በሚገኝ የሙስሊም መቃብር ስፍራ የተቀበረ አስከሬንን ቆፍረዋል የራስ ቅሉን ወስደዋል።
“ጠንቋዩ ከወንጀል ድርጊት የተገኘን ሐብት እንደሚካፈሉ ለሁሉም ቃል በመግባት የራስ ቅል እንዲፈልጉ ነግሯቸዋል” ሲል ዐቃቤ ሕግን ጠቅሶ ዴይሊ ፓንች የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
መስከረም መጀመሪያ ላይ ነበር ከ18 እስከ 28 ዕድሜ ያላቸው እነዚህ ወጣቶች በጠንቋዩ ትዕዛዝ መሠረት የራስ ቅሉን በሌላ ሦስተኛ ወገን አማካይነት ሲያጓጉዙ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉት።
- ‘የድመት ነፍስ አለው’ የሚባለው የሐማስ ወታደራዊ ኮማንደር ዴይፍ ማን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- “ቤታችንን በላያችን ላይ ቢያፈርሱትም የትውልድ ቀያችንን አንለቅም” የጋዛ ቤተሰቦችከ 5 ሰአት በፊት
- ቱርካዊት ሳይንቲስት የፈጠሩት ካንሰርን የሚመረምር ዘመናዊው ጡት መያዣከ 5 ሰአት በፊት
የናይጀር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ሚና የሚገኘው ፍርድ ቤት ግለሰቦቹን ለወንጀል በማሴር፣ የቀብር ቦታዎችን በማርከስ እና በሕገ-ወጥ መንገድ የሰው ራስ ቅልን በመያዝ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ለዚህ ሁሉ ድርጊት ዋነኛው ተጠያቂ የሆነው ጠንቋይ ግን አስካሁን ያልተያዘ ሲሆን፣ ክስም እንዳልተመሠረተበት ታውቋል።
በጁጁ ወይም በቩዱ ወይም በጥንቆላ ማመን በናይጄሪያ የተስፋፋ ልማድ ነው። ይህንንም በርካቶች ከክርስትና ወይም ከእስልምና ጋር አጣምረው እንደሚያካሂዱት በ2010 የወጣው የፒው የምርምር ማዕከል ሪፖርት ገልጿል።
በተመሳሳይ መንገድ በተለይም የሰው አካል ክፍሎች ገንዘብ ማስገኝት ይችላሉ በሚል በናይጄሪያ በቅርቡ ለተስፋፉት አስከፊ ግድያዎች ምክንያት ሆኗል።
ለዚህም በስፋት ዒላማ የሚደረጉት ደግሞ በቀላሉ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑትን ሕፃናት፣ ያላገቡ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን መሆኑ ታውቋል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ከሆነ የሰውነት ክፍሎች ሃብት ያስገኛሉ ተብሎ በሚታመንባቸው የአምልኮ ሥርዓቶች ለሽያጭ ይውላሉ።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ከ10 ሰዎች አራቱ በድህነት በሚኖሩባት ናይጄሪያ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የኢኮኖሚ መዳከም ገንዘብ ለማግኘት በሚል የሚከናወኑ የጥንቆላ ተግባራት ተስፋፍተዋል።
