ዴይፍ በጋዛ ጎዳናዎች ቢንቀሳቀስ እንኳ ማንነቱን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው
የምስሉ መግለጫ,ዴይፍ በጋዛ ጎዳናዎች ቢንቀሳቀስም ብዙዎች ማንነቱን ሊለዩት አይቸሉም

ከ 5 ሰአት በፊት

ሙሉ ስሙን ብዙ ሰው አያውቀውም። ይልቅ ቅጽል ስሙ ገናና ነው።

‘ዴይፍ’ ይባላል። ‘ዴይፍ’ ማለት ‘ጥቁር እንግዳ’ እንደማለት ነው፤ በአረብኛ።

ለምን ግን ‘ዴይፍ’ ተባለ?

ምክንያቱም በየሰዉ ቤት እየሄደ ስለሚያድር ነው። አንድ ቤት ከአንድ ሌሊት በላይ አያሳልፍም። እስራኤል በነፍስ ትፈልገዋለች። አንድ ቤት ሁለት ሌሊት ካደረ ከመልዓከ ሞት ጋር የማደር ያህል አደገኛ ነው ለእሱ።

ሞሳድ ይደርስበታል። ስለዚህ ሁሌ እንግዳ ነው፤ ጥቁር እንግዳ።

ዴይፍ የድመት ነፍስ ነው ያለው የሚባለው ለምንድነው ካልን መልሱ ማንም የሚገምተው ነው። እስራኤል ገደልኩት ስትል እየተነሳ፣ ሞተ ሲባል እያንሰራራ ስላስቸገረ ነው።

ኮማንደር ዴይፍ ላይ እስራኤል ተደጋጋሚ እና ተከታታይ የግድያ ሙከራ ብታደርግበትም አልተሳካላትም። አራት ጊዜ ገደልኩት ብላ አራት ጊዜም ቆስሎ አምልጧል።

አንድ ጊዜ ዐይኑን አጥፍታዋለች። አንድ ጊዜ እግሩን አሳጥታዋለች። ሌላ ጊዜ መላ ቤተሰቡን በቦምብ ገድላለች።

ዴይፍ ግን ሞተ ሲባል የሆነ ቦታ ብቅ ይላል። “እስራኤል ወዬሁልሽ” እያለ መግለጫ ይሰጣል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ለእስራኤል ማስጠንቀቂያ በድምጽ ላከ። በፍልስጤማውያን ሕይወት መቀለድ የማታቆም ከሆነ ቅጣት እንደሚጠብቃት የሚገልጽ መልዕክት።

በቀናት ውስጥ 13 እስራኤላዊያን ተገደሉ። እሰራኤል በበኩሏ 242 ሰዎችን በጋዛ ገደለች። ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚሆኑት አሸባሪዎች ናቸው ብላ ነበር። እስራኤል ከነዚህ አሸባሪዎች አንዱ መሐመድ ዴይፍ እንደሆነ ጭምር አምና ነበር።

ዴይፍ ግን ትንሽ ቆይቶ “አለሁ አልሞትኩም” ብሎ መጣ።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የነበሩት ዲሰይ ዚልበርማን “በኦፕሬሽኑ ጊዜ በሙሉ መሐመደ ዴይፍን ለመግደል ሞክረናል፤ አልተሳካልንም እንጂ” ብለው ነበር ያኔ ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ።

ዴይፍ ለዓመታት አድፍጦ በድጋሚ የእስራኤል ራስ ምታት ሆነ።

ከሳምንት በፊት ዓለምን ያነጋገረው እና በእስራኤል ላይ የደረሰውን ድንገተኛ ጥቃት ያቀነባበረው ይኽው መሐመድ ዴይፍ ሳይሆን እንዳልቀረ ይነገራል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የተፈጸመውን መብረቃዊ ጥቃት ተከትሎ በሰዓታት ውስጥ በሐማስ ቴሌቪዥን መሐመድ ዴይፍ ደንገዝገዝ ባለ ብርሃን ውስጥ ሆኖ ብቅ በማለት “የእስራኤል ግፍ በቃን። የአል አቅሳው ጎርፍ ዘመቻ መብረቃዊ ጥቃትን ጀምረናል” ሲል አወጀ።

በዚህ መሐመድ ዴይፍ አቀነባበረው በተባለው የማይታመን ጥቃት፣ ይህ ዘገባ እስኪጠናቀር ድረስ ከ1400 በላይ እስራኤላውያን ተገድለዋል። ከሟቾቹ ውስጥ ጥቂት የሌላ አገር ዜጎችም ይገኙበታል።

ከ150 በላይ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሐማስ ታጣቂዎች ታግተው ወደ ጋዛ ሰርጥ ተወስደዋል።

መሐመድ ዴይፍ ማን ነው?

ዴይፍ በጋዛ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ ዋና አዛዥ ነው
የምስሉ መግለጫ,ዴይፍ በጋዛ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ ዋና አዛዥ ነው

ስለዚህ ሰው ልጅነት ብዙም አይታወቅም። እውነተኛ ስሙ ግን ይታወቃል። ዲያብ ኢብራሒም አልማስሪ ነው።

አንዳንድ ሚዲያዎች ዴይፍ የተወለደው በጋዛ የስደተኛ ካምፕ ውስጥ በ1960ዎቹ ነው ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ሌላ ይላሉ።

ስለ ዴይፍ ልጅነት ከዚህ የዘለለ ብዙም አይታወቅም። ሐማስን የተቀላቀለው በወጣትነቱ ምናልባትም የመጀመሪያውን የፍልስጤማውያን አመጽ (ኢንቲፋዳ) ተከትሎ ነው።

እስራኤል ዴይፍን በ1989 (እአአ) በቁጥጥር ሥር አውላው ነበር። ሁለት ዓመት ግድም ታስሮ ተፈታ።

ከእስራኤል ስቃይ የበዛበት እስር በኋላ ግን ዴይፍ ሌላ ሰው ሆነ።

በሐማስ የውስጥ ሥልጣን መሰላል ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ላይ ወጣ። የሐማስ ወታደራዊ ክንፍን አጠናከረው።

ተከታታይ የሆኑ የሽብር ጥቃቶችን አቀነባብሯል ይላሉ ተንታኞች። ከፈረንጆቹ 1995 ወዲህ የተፈጸሙትን ብዙዎቹን የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች ያቀነባበረው እሱ ሳይሆን አይቀርም ይባላል።

በመጨረሻ ዴይፍ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነውን አልቃሳም ብርጌድን በአዛዥነት መምራት ጀመረ። ይህም በአውሮፓውያኑ በነሐሴ 2002 የሆነ ነው።

ይህን ከፍተኛ ሥልጣን የተቀዳጀው እስራኤል ዕውቁን የቡድኑን አዛዥ ሳሊህ ሸሐዳን ከገደለች በኋላ ነበር። ሳሊህ የአልቃሳም ዋና አዛዥ ነበር።

እሱን ለመግደል የተደረጉ 7 ሙከራዎች

በአውሮፓውያኑ 2000 መባቻ ላይ አራት ተከታታይ የግድያ ሙከራዎችን አምልጧል። በእነዚያ የግድያ ሙከራዎች ምክንያት ነው አንድ ዐይኑን ያጣው።

አንድ የእስራኤል የደኅንነት ሰው በ2006 ዴይፍ እንደተገደለ እምነት እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምስተኛው የግድያ ሙከራ የተደረገበት በ2014 (እአአ) ነበር። እስራኤል እሱን ለመግደል በጋዛ ሼክ ሬድዋን በሚባለው ሰፈር ጅምላ የአየር ጥቃት መፈጸም ነበረባት።

ዴይፍ ከዚህ ጥቃትም በተአምር አመለጠ። ከጥቃቱ ማምለጥ ያልቻሉት ዊዳድ የተባለችው ባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ተገደሉ።

አንዳንድ የእስራኤል የደኅንነት ሰዎች ቆስሎ ነው ያመለጠው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ጭራሽ በወቅቱ እዚያ አልነበረም ይላሉ።

ከዚያ በኋላ ሌሎች ሦስት የግድያ ሙከራዎችን አምልጧል።

ኔታንያሁ “ሁሉም የሐማስ አባል የሞት ጥላ እየተከተለው ነው” ሲሉ አሁን እያደረጉ ባለው ዘመቻ አንድም ሰው እንደማይተርፍ ዝተዋል።

ከዚህ ዛቻ የሚተርፍ አንድ የሐማስ አመራር ካለ ምናልባት ዴይፍ ሊሆን ይችላል። ለመሆኑ በእስራኤል የደኅንነት ተቋማት እና ወታደራዊ ኃይሎች ከተቀነባበሩበት የግድያ ሙከራዎች እንዴት ሊያመልጥ ቻለ?

አንድ የደኅንነት ጉዳዮች አዋቂ ለቢቢሲ ሲናገሩ ዴይፍ ለእስራኤል አልጨበጥ ያለው ከማንኛውም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራሱን ስላራቀ ነው ይላሉ።

“ስልክ ከሌለህ፣ ኮምፒውተር ካልተጠቀምክ፤ ዘመናዊ የስለላ መረብ ሊያጠምድህ እንዴት ይቻለዋል?” ብለው ይጠይቃሉ እኚህ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ።

ሌላ የእሰራኤል የቀድሞ የደኅንነት ሰው ደግሞ ሐማስ ጥልቅ የመሬት ለመሬት ዋሻዎችን ቆፍሮ አዛዦቹን ስለሚያኖር፣ እንዲሁም ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ንጹሐንን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ስለሚንቀሳቀሱ ዴይፍ ከተደገሰለት ሞት ሊያመልጥ ችሏል ብለው ያምናሉ።

ዴይፍ በአደባባይ አይታይም። ጋዛ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው አይተው የሚለዩት። ነገር ግን “ጀግና” የሚሉት ልጃቸው ነው። ድል ባደረጉ ቁጥር ስሙን ከፍ አድርገው ያወሱታል።

እስራኤል በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ በዴይፍ ላይ ብቻ ሰባት ጊዜ የግድያ ሙከራ አድርጋለች። አካሉን ከማጉደል ውጪ አንዱም የሐማሱን ቁልፍ ሰው እስትንፋስ ሊቆርጥ አልቻለም።

አሁን አሜሪካ ዴይፍን በአደገኛ የአሸባሪዎች ዝርዝር መዝገብ ላይ አስፍራዋለች።

እስራኤል አሁንም ከማንም በላይ ዴይፍን ትፈልገዋለች። ከተቻለ በነፍስ ካልተቻለ ደግሞ የተረፈ ዐይኑን፣ የተረፈ እግሩን ልታጠፋ ትሻለች።

ሐማስ በተቀናጀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ከባድ ጥቃት የተቆጡት እስራኤላውያን እና ባለሥልጣናቷ ቡድኑን እና መሪዎቹን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ዝተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ዴይፍ ዋነኛው ኢላማዋ ነው። እስራኤል በስለላ እና በወታደራዊ ተቋሞቿ አማካይነት ከዚህ ቀደም ከሞከረችበት የግድያ ሙከራዎቿ የተረፈውን ዴይፍን በጥብቅ ትፈልገዋለች።

በዚህም ምክንያት ዴይፍ ከዚህ ወዲያ በሕይወት ላይቆይ ይችላል። ድመትም ብትሆን 9 ነፍስ ነው ያላት።