ገንዘብ የያዘች ሴት እጅ

18 ጥቅምት 2023, 14:02 EAT

የናይጄሪያ መንግሥት 15 ሚሊዮን ለመሆኑ ችግረኛ ቤተሰቦች 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማከፋፈል እንደሚጀምር አስታወቀ።

ይህ መንግሥት ለድሆች ለመስጠት ያቀደው የገንዘብ ድጎማ በአገሪቱ እየናረ የመጣውን የምግብ፣ የነዳጅ እና የሸቀጦች ዋጋ ለማቅለል በማለም ነው ተብሏል።

ይህ ድጎማ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ድጋፉ ይገባዋል ለሚባል ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ከዚህ ጥቅምት ወር ጀምሮ በየወሩ ገንዘቡ ይሰጣል።

ለድሆች የታሰበው ድጎማ ለሦስት ወራት የሚዘልቅ ሲሆን እያንዳንዱ ቤተሰብ በወር 25,000 ናይራ (የናይጄሪያ ገንዘብ) ወይም 32 ዶላር በጥሬ ገንዘብ ያገኛሉ።

ይህን ለድሆች የሚሰጥ የመንግሥት ድጎማ እንደሚጀመር ይፋ የሆነው የናይጄሪያ የገንዘብ ሚኒስትር ዋለ ኢዱን በዋና ከተማዋ አቡጃ ውስጥ በተሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

ከ200 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ባላት ናይጄሪያ የመንግሥትን ድጎማ የሚያገኙት 15 ሚሊዮን ቤተሰቦች 62 ሚሊዮን ናይጄሪያውያንን ያያዙ መሆናቸውን መንግሥት አስታውቋል።

ፕሮግራሙ ሐምሌ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገለጽ ለ12 ሚሊዮን ቤተሰቦች 10 ዶላር ለመስጠት መታቀዱ ተነግሮ ነበር።

ነገር ግን ገንዘቡ በቂ አይደለም የሚል ትችት ከሕዝቡ በኩል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ለዚህ ምላሽም ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በተከበረው የነፃነት ቀን ላይ አዲስ ዕቅድ እንደሚተገበር አሳውቀው ነበር።

ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በሦስት ወራት ውስጥ የሚሰጠው 75,000 ናይራ የድሃ ቤተሰቦችን አቅም የሚያነቃቃ፣ ምግብ እንዲያገኙ የሚስችል እና ልጆቻቸው ቢያንስ ወደ መሠረታዊ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ያስችላል ብሎ መንግሥት እንደሚያስብ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ግንቦት ወር ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት መንግሥት ይሰጥ የነበረውን የነዳጅ ድጎማ በማንሳታቸው ብዙ ናይጄሪያውያን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያጋጠማቸው ነው።

መንግሥት የነዳጅ ድጎማን በማንሳቱ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ያወጣውን 10 ቢሊየን ዶላር የሚያድንለት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ናይጄሪያ ውስጥ ባለፉት ተከታታይ ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የተመዘገበ ሲሆን፣ መስከረም ወር ላይ የነበረው የግሽበት መጠን 26.7 በመቶ ሲደርስ፣ የምግብ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪም 30.6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው የናይጄሪያ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ እንደገለጸው ከሆነ 63 በመቶ ያህሉ ናይጄሪያውያን “በዘርፈ ብዙ ድህነት” ውስጥ እንዳሉ አስታውቋል።