ኮሜዲያን ልጅ ያሬድ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ መታዘዙ ተገለፀ።
ያሬድ ዘላለም በቅጽል ስሙ “ልጅ ያሬድ” እየተባለ የሚጠራው ኮሜዲያን በቀረበበት ተደራራቢ ክስ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዟል።
ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ የፀረ-ሽብርና የሕገ-መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን ፥ የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ኮሜዲያኑ ላይ ተደራራቢ ክሶችን ማቅረቡም ተገልጿል።
ዐቃቤ ህግ በኮሜዲያን ልጅ ያሬድ ላይ ካቀረባቸው ክሶች ውስጥ፥ በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም በማጉደፍ፣ ጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ነጥቦች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
ኮሜዲያን ልጅ ያሬድ ክሱ ከደረሰው በኋላ ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄው ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ታዟል።
ተከሳሹ ችሎት በቀረበበት ጊዜ ዐቃቤ ሕግ ለቤተክርስቲያን ክብር፣ ለማህበረሰቡ ስነልቦና፣ እሴትና ባህል ሲባል በክሱ ላይ የቀረቡ ዝርዝር ነጥቦች እንዳይታተም በሚዲያ እንዳይቀርብ እንዲሁም ችሎቱ በዝግ እንዲሆን አቤቱታ አቅርቧል።
አቤቱታውን የመረመረው ፍርድ ቤቱም የማህበረሰቡን ክብርና ስነልቦናን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ እንዳይሰራጭ ችሎቱ በዝግ እንዲሆን ብይን ሰጥቷል።
[ኤፍ ቢሲ ፣ ታሪክ አዱኛ]
