በ12ኛ ክፍል ውጤት “ራቁታችንን ምን እንደምንመስል አይተነዋል” – ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የመስሪያ ቤታቸውን የዘንድሮ እቅድ እና የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ለማቅረብ ዛሬ ረቡዕ በፓርላማ ተገኝተው ነበር። የዛሬውን ስብሰባ በጠራው የተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሚኒስትሩ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን የሚመለከተው ይገኝበታል።
የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄዎች በንባብ ያሰሙት የፓርላማ አባል “በተከታታይ ለሁለት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት በጣም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? ትምህርት ሚኒስቴር የፈተናውን ውጤት እንዴት ያየዋል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ፕ/ር ብርሃኑ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “የ12ኛ ክፍል ውጤት እንደዚህ መሆን፤ ምንምን እንኳ really መጠበቅ የነበረን ነገር ቢሆንም ሁላችንንም አስገርሞናል” ብለዋል።
“የፈተናውን አሰጣጥ መቀየር ብቻ ይሄን ካሳየ፤ ከዚህ ተነስተን ብቸኛ ነገር ልንል የምንችለው፤ ከዚያ በፊት ስንሰጣቸው የነበሩ ፈተናዎች በሙሉ የተማሪን እውነተኛ ችሎታ የሚያሳዩ አይደሉም ማለት ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ይሰጡ በነበሩ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በትምህርት ቤቶች እና በክልል ደረጃ ሳይቀር በተደራጀ መልኩ “ፈተናዎች የሚሰረቁበት” እንደነበር የጠቀሱት ፕ/ር ብርሃኑ፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ውጤቶች የተማሪዎችን ችሎታ የሚያንጸባርቁ እንዳልነበር አስረድተዋል።
“አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ refelect አድርጎልናል። አሁን የምንደበቅበት ቦታ የለም። ሰርቀን የምናሳይበት ቦታ የለም። ራቁታችንን ምን እንደምንመስል አይተነዋል” ሲሉም የትምህርት ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
