October 18, 2023 – EthiopianReporter.com


ዜና ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከናይል ፕሮሞሽን ጋር ሲከራከር የከረመበትን የክፍያ ክስ…
ቀን: October 18, 2023
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከአምስት ዓመታት በፊት የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ አቅርቦት ከነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት ጋር በተያያዘ፣ ናይል ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በክፍያ ምክንያት ሲያደርጉት የከረሙትን የፍትሐ ብሔር ክርክር ክስ አሸነፈ፡፡
ቴዲ አፍሮ ‹‹ወደ ፍቅር ጉዞ›› የሚለውን ኮንሰርት በመስቀል አደባባይ ለማቅረብ ከናይል ፕሮሞሽን ጋር የተስማማው አሥር ሚሊዮን ብር እንዲከፈለው ቢሆንም፣ ኮንሰርቱ ከተካሄደ በኋላ ኩባንያው ‹‹የምከፍልህ ሁለት ሚሊዮን ብር ብቻ ነው›› በማለቱ፣ ጉዳያቸው በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን የፍርድ ሰነዱ ያስረዳል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክሱን ሲመረምር ከሦስት ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡
ድምፃዊው በጠበቆቹ አማካይነት ባቀረበው ክስ፣ ‹‹ወደ ፍቅር ጉዞ›› የተሰኘውን ኮንሰርት ለማዘጋጀት ከናይል ፕሮሞሽን ጋር ውል የገቡት አሥር ሚሊዮን ብር ሊከፍለው ተስማምተው ሲሆን፣ ስምምነቱም አምስት ሚሊዮን ብር በቃልና አምስት ሚሊዮን ብር ደግሞ በተዘጋጀ ሰነድ መፈጸማቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ኮንሰርቱ ከተካሄደ በኋላ፣ ናይል ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ክፍያ እንዲፈጽም ሲጠየቅ፣ መክፈል ያለበት ሁለት ሚሊዮን ብር መሆኑን በመግለጽ ሌላውን እንደማይመለከተው በማሳወቁ፣ ጉዳዩ ወደ ክስ አምርቶ ለሦስት ዓመታት ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል፡፡
ጉዳዩን ሲመረምር የከረመው ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ፣ ናይል ፕሮሞሽን ክፍያ ለመፈጸም በሰነድ ላይ የተስማማው አምስት ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ መክፈል ያለበት በውሉ መሠረት መሆኑን ጠቅሶ ክፍያ እንዲፈጽም፣ ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቷል፡፡
